የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስቀድሞ በተቀመጠው ቀን ይጀመራል ተባለ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ ሊጉ አስቀድሞ በተያዘለት ቀን መሠረት ኅዳር 13 እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን በይፋ ከመጀመሩ በፊት በተለያዩ የክልል ከተሞች ክለቦች ራሳቸውን የሚመለከቱባቸው የአቋም መፈተሻ ውድድሮች ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል፤ 8 ክለቦች የሚሳተፉበትና በአዲስአበባ እግርኳስ ፌደሬሽን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ በተለይ ከሰሞነኛ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስቀድሞ ከተያዘለት የመጀመሪያ ቀን በአንድ ሳምንት በማራዘም በመጪው ጥቅምት 29 እንደሚጀመሩ በቅርቡ መገለፁ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሠረት የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የደረጃና የፍፃሜ ጨዋታዎች በህዳር 13 እና 14 እንደሚካሄዱ መርሃግብር የተያዘላቸው ሲሆን በአንጻሩ የአዳማና የትግራይ ዋንጫ አስቀድመው ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ከፕሪምየር ሊጉ መጀመሪያ ቀን ጋር የሚገጥም በመሆኑ ዐቢይ ኮሚቴው ውድድሩ ከዚህ ቀን አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ አሳስቧል፡፡

በተያያዘም በመጪው ኅዳር አምስት ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ክለቦች በተገኙበት የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት እንደሚከናወን አያይዞ የዐቢይ ኮሚቴው በዛሬው መደበኛ ስብሰባው መወሰኑ ተገልጿል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: