ፌዴሬሽኑ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ድልድል ዙርያ ሀሳቡን ሲቀይር የዝውውር መስኮቱን አራዝሟል

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዝውውር መስኮት ጥቅምት 25 ይዘጋል ተብሎ ቢጠበቅም በተሳታፊ ክለቦች ጥያቄ መሠረት ወደ ህዳር 8 መራዘሙን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። አስቀድሞ አውጥቶ ለክለቦች የበተነው የምድብ ድልድልንም ወደፊት በሚገለፅ ቀን በእጣ ለማድረግ መወሰኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሁለተኛው የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 36 ክለቦች በሶስት ምድብ ተከፍለው ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉበት ውድድር መሆኑ ይታወቃል ፤ ነገርግን ውድድሩ ገና ከጅምሩ የቀን ለውጦችን እያስተናገደ ይገኛል። ፌደሬሽኑ ለተሳታፊ ክለቦች በላከው መልእክትም አስቀድሞ ጥቅምት 25 ይጠናቀቃል የተባለው የ2012 ውድድር ዘመን የክለቦች ክፍያና የአዳዲስ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ምዝገባ እስከ ህዳር 8 ተገፍቷል።

በተያያዘም ለክለቦች በተላከው መልእክት ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የየምድቦቹ ተሳታፊ ቡድኖች በግልፅ ደብዳቤ ሰለመላኩ እየታወቀ ፌደሬሽኑ የምድብ ድልድሉ እንዳልወጣ በይፋ መገልፁ አግራሞትን ያጫረ ጉዳይ ሆኗል።

በተጨማሪም በቅርቡ ለክለቦች በተላከው የምድብ ድልድል ዙሪያ አንዳንድ የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ከወዲሁ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛል፤ የክለቦቹ ጥያቄም የ2011 የውድድር ዘመን ግምገማ ሳይደረግና ክለቦች በጋራ ተገኝተው ሀሳባቸው ባላቀረቡበት ሁኔታ ፌዴሬሽኑ ክለቦችን ባላሳተፈ ሁኔታ ድልድሉን ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለክለቦች የምድብ ድልድሉን ማሳወቁን የሚገልፅ ደብዳቤ (ምድብ ለ)

ቅሬታዎቹን መሠረተ ቢስ ለማስመሰል ፌዴሬሽኑ ለክለቦች ክፍያን ባሳወቀበት መልእክት አባሪ በማድረግ የላከውን መልእክት ወደ ጎን በመተው “እንዳንድ ሚድያዎች የዘገቡት ዘገባ ስህተት ነው፤ የተላከ የምድብ ድልድል የለም።” በማለት ያቀረበው ሀሳብ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አያይዘው ክለቦቹ ገልፀዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ