አዳማ ዋንጫ | አስተናጋጁ ክለብ ጅማን አሸንፏል

በመክፈቻው ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ከእረፍት መልስ ተነቃቅቶ የቀረበው አዳማ ከተማ ጅማ አባጅፋርን 2-0 ማሸነፍ ችሏል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አዳማ ከተማ የተሻለ ቢንቀሳቀስም የጠሩ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ሲቸገሩ ተስተውሏል። ደካማ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ቡልቻ ሹራ በ6ኛው ደቂቃ ቋሚ ከመለሰበትና በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ወቅት የኃላሸት ፍቃዱ ካመከናቸው ኳሶች ውጭ ተጠቃሽ ሙከራ ያላስመለከተ አጋማሽ ነበር። ጅማዎች እጅግ ደካማ በነበሩበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ አዳማ የግብ ክልል መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽን የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የተለዩ ሆነው ቀርበዋል፤ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በዳዋ ሆቲሳና ሀይሌ እሸቱ ጠንካራ ሙከራ በማድረግ የጀመሩት አዳማዎች እንደአዲስ እየተዋቀረ የሚገኘውን ጅማ አባጅፋር ቡድን ተጫዋቾች ከፍተኛ ፈተና ሆነው ታይተዋል።

በ59ኛውና በ61ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሱሌይማን ሰሚድና ሀይሌ እሸቱ ከጅማ ተከላካዮች ጀርባ የተጣለላቸውን ኳስ ተጠቅመው ከበረኛ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝተው በሁለቱም አጋጣሚ በረኛውን በማለፍ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
በ66ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰሠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቲሳ መትቶ አዲሱ ጋናዊው የጅማ ግብጠባቂ አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተስፋዬ ነጋሽ በግሉ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ተከላካይነት ሚና በማጥቃቱም በመከላከሉም ድንቅ አጋማሽ ማሳለፍ ችሏል።

ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱበት ተሂደት የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም በቂ መብራት ስላልተገጠመበት ለጨዋታ አስቸጋሪ ሆኖ ተስተውሏል፤ ጨዋታውም ተጨማሪ የሚጠቀስ ነገር ሳይታይበት በአዳማ የ2ለ0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ