የደቡብ ሠላም ዋንጫ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ነገ ይጀምራል

በከፍተኛ ሊግ ክለቦች መካከል የሚደረገው የደቡብ ክልል ሠላም ዋንጫ ነገ በሀላባ ከተማ አዘጋጅነት ይጀመራል።

ለአራተኛ ጊዜ የሚደረገው ይህ ውድድር በካስቴል ቢራ ስፖንሰርነት ያለፉትን ሦስት ዓመታት ሲደረግ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ መጠሪያ ስያሜው ላይ ለውጥ በማድረግ ደቡብ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የሠላም ዋንጫ ወደሚል በመሸጋገር ከነገ ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት እየተደረገ ይቆያል።

በውድድሩ ላይ በክልሉ የሚገኙ አስራ ሁለት ክለቦች ተካፋይ ይሆናሉ ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እክል በመሆናቸው ስድስት ክለቦችን ብቻ ያሳትፋል ሲሉ አቶ ደመላሽ ይትባረክ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ሀላባ ከተማ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ቡታጅራ ከተማ፣ ዲላ ከተማ፣ ከምባታ ሺንሺቾ እና እስካሁን ምላሽ ያልሰጠው ደቡብ ፖሊስ በውድድሩ ይሳተፋሉ ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዕጣ ማውጣት ስነስርአቱ ዛሬ አመሻሽ ከወጣ በኃላ ነገ ከሰዓት በሚደረግ የመክፈቻ መርሀግብር ውድድሩ ይጀምራል፡፡

ዘንድሮ ሊደረግ ታስቦ የነበረው እና ባለፉት ተከታታይ አመታት የተከናወነው በፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል ይደረጋል ተብሎ የነበረው ውድድር ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ