አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል

የወልዋሎው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከገጠማቸው መጠነኛ የጤና እክል አገግመው ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል።

በደረሰባቸው መጠነኛ የጤና እክል ምክንያት ላለፉት ሳምንታት ከስራ ገበታቸው ተለይተው የቆዩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአዲስ አበባ ዋንጫ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ቡድናቸውን የመሩ ሲሆን አሁን ላይ ጤናቸው ወደ ጥሩ ሁኔታ መመለሱን ተከትሎ ወደ ስራቸው ተመልሰው በትናንትናው ዕለት ልምምድ ማሰራት መጀመራቸው ሲረጋገጥ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ወልዋሎን ማሰልጠን የጀመሩት አሰልጣኙ በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ከወልዋሎ ጋር ውላቸው ማራዘማቸው ሲታወስ በቀጣይ የውድድር ዓመትም በአዲስ ስብስብ ወደ ውድድር የሚገቡ ይሆናል።

በርካታ ተጫዋቾች አስፈርመው አምስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጉት ወልዋሎዎች ከአዲስ አበባ ዋንጫ መልስ በቀጣይ ቀናት ወደ መቐለ ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ