የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ጥር ወር ሲመለስ የማጣርያ ጨዋታ ቀናትም ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል

የ2021 አፍሪካ ዋንጫ በአየር ሁኔታ ምክንያት ጥር ወር ላይ እንዲካሄድ ሲወሰን በዚህም ምክንያት የማጣርያ ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ቀናት ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል።

የአህጉሪቱ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል ካፍ በደረሰበት ውሳኔ መሠረት ካሜሩን የምታስተናግደው የ2021 ውድድር በሰኔ ወር ላይ በሀገሪቱ ከሚኖረው ከፍተኛ ዝናብ ጋር በተያያዘ ወድድሩን ማከናወን አስቸጋሪ ስለሚሆን ከዚል ቀደም ወደነበረበት የፈረንጆች ዓመት መጀመርያ መቀየሩን አስታውቋል። በዚህም ከጥር 1 እስከ ጥር 29 ድረስ የሚከናወን ይሆናል።

አህመድ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ አነጋጋሪ ለውጦችን እያስተናገደ የሚገኘው ካፍ የአህጉሪቱን ትልቅ ውድድር ወደ ሰኔ ወር ሲያሸጋግር በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት በክረምት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባና ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ጋር ለማጣጣም ነው በሚል በስፋት ሲተች መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ከለውጡ በኋላ አንድ ውድድር (2019/ግብፅ) ብቻ አድርጎ በአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ጥር መመለሱ አነጋጋሪ ሆኗል።

የአፍሪካ ዋንጫ በጥር ወር እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ በረጅም ወራት ልዩነት እንዲከናወኑ የወጡት መርሐ ግብሮች ውድድሩን ባማከለ መልኩ ተሸጋሽገዋል። እስካሁን ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉበት የምድብ ማጣርም ውሳኔውን ተከትሎ በአዲስ መርሐ ግብር ተለውጧል።

3ኛ እና 4ኛ የምድብ ጨዋታዎች

(ኢትዮጵያ ከኒጀር ጋር በተከታታይ ትጫወታለች)

ቀድሞ የነበረው ፡ ከነሀሴ 25 – ጳጉሜ 4

አዲሱ
: ከመጋቢት 14 – 22

5ኛ የምድብ ጨዋታዎች

(ኢትዮጵያ ከማዳጋስካር በሜዳዋ ትጫወታለች)

ቀድሞ የነበረው ፡ ከመስከረም 25 – ጥቅምት 3

አዲሱ
: ከግንቦት 24 – ሰኔ 2

6ኛ የምድብ ጨዋታዎች

(ኢትዮጵያ ከ አይቮሪኮስት ከሜዳዋ ውጪ ትጫወታለች)

ቀድሞ የነበረው ፡ ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 8

አዲሱ
: ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 3


© ሶከር ኢትዮጵያ