“ዩጋንዳ ላይ የነበረውን ቁጭት ነገ በደጋፊዎቻችን ፊት እንወጣለን” የ U-17 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ

ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የመልስ ጨዋታ የሚያደርገው ቡድኑ ስለ ዝግጅት ጊዜ እና ስለ ነገው ጨዋታ በዋና አሰልጣኙ እና በአምበሉ አማካኝነት መግለጫ ሰጥቷል።

በህንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ 10:00 የዩጋንዳ አቻውን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ያስተናግዳል። ይህንን ጨዋታ አስመልክቶ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ እና የቡድኑ አምበል ቤቲ ዘውዱ ሀሳባቸውን ለጋዜጠኞች አካፍለዋል።

በቅድሚያን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ በአጭሩ የሚከተለውን ብሏል። “ከፊታችን ላለው የነገ ጨዋታ ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ እያከናወንን እንገኛለን። ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ የነበሩን የልምምድ ጊዜያት ሰፋ ያሉ ስለነበሩ ብዙ ሥራዎችን ሰርተናል። ባህር ዳር ከገባን ጊዜ ጀምሮ በመጀመሪያው ጨዋታ የሰራናቸውን ስህተቶች ለማረም ስንጥር ነበር። በተለይ ደግሞ ግብ አካባቢ የነበሩብንን ችግሮች ለመቅረፍ ሞክረናል። ፊት መስመር ላይ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም ጠንክረን ስራዎችን ሰርተናል። በአጠቃላይ እኛ ያለብንን አደራ ለመወጣት በዝግጅት ላይ እንገኛለን።”

ከአሰልጣኙ በመቀጠል የቡድኑ አምበል ቤቲ ዘውዱ ሀሳቧን በአጭሩ ገልፃለች። ” የነገውን ጨዋታን አስመልንቶ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዳችንን ሰርተናል። በድክመቶቻችን ላይ ትኩረት አድርገን ልምምዶችን ስንሰራ ቆይተናል። ሁላችንም ተባብረን ከነገው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ቆርጠን ተነስተናል።”

በመቀጠል በቦታው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቷል።

ስለ መጀመሪያው ጨዋታ

እንደገለፅኩት ከመጀመሪያው ጨዋታ ተነስተን ነው ልምምዶችን ስንሰራ የነበረው። በመጀመሪያው ጨዋታ ትንሽ የጎዳን ተጨዋቾቻችን ልምድ አለመኖራቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የተከላካይ ክፍላችን የነበረበት የመዘናጋት ችግር እና አጥቂዎቻችን አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ግቦችን አለማስቆጠራቸው ዋጋ አስከፍሎናል። በዋናነት ግን በመጀመሪያዎቹ እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበሩብን የትኩረት ማነስ ችግር እንድንሸነፍ አድርጎናል።

ከተጋጣሚያቸው መነሻነት ስለሰሩት ልምምድ

በመጀመሪያው ጨዋታ ዩጋንዳዎች በረጃጅም ኳሶች እና በመስመር ሲያጠቁን ነበር። ይህንን በደንብ ተመልክተን በልምምድ መርሃ ግብራችን ስራዎችን ሰርተናል። በተለይ ረጃጅም ኳሶች እንዳይጣሉ መንገዶችን ስንፈጥር ነበር። ረጃጅም ኳሶች ቢመቱብን እንኳን እንዴት እንከላከላለን የሚለውን በደንብ ተነጋግረናል። በአጠቃላይ ከእኛ መነሻነት ብቻ ሳይሆን ከእነሱም ጠንካራ ጎን ተነስተን ልምምዶችን ሰርተናል።

ስለ ቡድኑ አላማ

ዋና አላማችን ቡድኑ መሰረት እንዲኖረው ነው። ፌደሬሽናችን ከታችኞቹ ቡድኖች ጀምሮ እስከ ሉሲዎቹ ድረስ መተካካቶች እንዲኖሩ ስለሚፈልግ ይህንን ለማድረግ ነው የምንጥረው። ይህ ማለት ግን ውጤት አንፈልግም ማለት አደለም። እንደ ቡድን ውጤት ማምጣት ስላለብን ውጤቱን እንፈልገዋለን። ዩጋንዳ ላይ ቁጭት ነበረብን። ስለዚህ ነገ በደጋፊዎቻችን ፊት ቁጭታችንን እንወጣለን።

አዲስ ስለተቀላቀሉ ተጨዋቾች

ቡድናችንን ያጠናክራሉ ብለን ያሰብናቸውን ሶስት ተጨዋቾች ወደ ቡድናችን ቀላቅለናል። የቀላቀልናቸው ተጨዋቾች ከዚህ ቀደም ተጫውተው ስለሚያውቁ እና ልምድ ስላላቸው ይጠቅሙናል። እኛ ተጨዋቾቹን ስናመጣ ዝም ብለን አደለም ያመጣነው። በሚጎለን ቦታ ላይ ነው ተጨዋቾቹን ያመጣነው።

ዛሬ ማለዳ 1 ሰዓት በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ያከናወነው ቡድኑ ሁሉም ተጨዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል። ነገርግን በዛሬው የልምምድ መርሃ ግብር የቡድኑ ቁልፍ የተከላካይ መስመር ተጨዋች ነፃነት ፀጋዬ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟት ታይቷል።

የስታዲየም መግቢያ ዋጋ እንደሌለ እና የባህር ዳር እና አካባቢው የስፖርት ቤተሰብ በነፃ ወደ ስታዲየም ገብቶ ቡድኑን እንዲያበረታታ ተጠይቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: