“ተስፋዬ ኡርጌቾ እና የግንቦት ወር ግጥጥሞሽ” ትውስታ በገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ተስፋዬ ኡርጌቾ ዛሬ በትውልድ ከተማው ወንጂ ኪዳነ ምህርት ቤተክርስቲያን ግብዓተ መሬቱ ተፈፅሟል። የዚህ ዘመን ትውልድ ተስፋዬ ኡርጌቾ ማን እንደሆነ እንዲያውቅ በማሰብ የተለያዩ ዘገባዎችን እንደምናቀርበ በተናገርነው መሰረት በትውስታ አምዳችን ተስፋዬ ኡርጌቾ እና የግንቦት ወር ግጥጥሞሽን አስመልክቶ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) አጫውቶናል።

“በ1983 በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ሰባተኛው አፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ አሰልጣኝ ካሣሁን ተካ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ በግብፅ ሊያቀኑ በዝግጅት ላይ ናቸው። ከጉዞው አስቀድሞ 22 ተጫዋቾች ስብሰባ ያደርጋሉ። ግብፅ ደርሰው እንዴት እንደሚጠፉ፣ እንዴት የፖለቲካ ጥገኝነት እንደሚጠይቁ እና የአጠፋፉን ሁኔታ የተመለከተ ስብሰባ አድርገዋል። የእነዚህ አጠፋፍ ከሌላው ጊዜ የሚለየው ከዚህ ቀደም አንዱ ለአንዱ ሳይነጋገር ነበር በሄዱበት ሀገር ይጠፉ የነበሩት። እነዚህ ግን ከመጥፋታቸው ሰምንት ቀን አስቀድሞ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስብሰባ አድርገው ዋና ሰብሳቢ፣ ዋና ፀሐፊ እንዲሁም ኮሚቴ በድምፅ ብልጫ መርጠው የጠፉ መሆናቸው ነው። በስብሰባቸው ወቅት ሰባቱ ተጫዋቾች አንጠፋም ሄደን እንመለሳለን ይላሉ። እነዚህም ፉአድ፣ ቡልቻ፣ ጫኔ፣ ሰለሞን እና የአሁኑ የጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) ይገኙበታል። 14 ተጫዋቾች ደግሞ ሄደን አንመለስም በዛው እንጠፋለን ይላሉ። በዚህ ሰዓት ተስፋዬ ኡርጌቾ ሰባታችሁ አንጠፋም ካላችሁ እኔ ከአስራ አራቱ ጎራ እቀላቀላለው ብሎ አስራ አምስተኛ የሚጠፋ ተጫዋች በመሆን ተስማምቷል።

ከመሔዳቸው አስቀድመው እቅድ ያወጡት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ያሰቡት አልቀረ ሳይበታተኑ አንድ ላይ ሆነው ግብፅ ላይ ይጠፋሉ። ከጠፉትም መካከል አፈወርቅ (ካቻ)፣ ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ)፣ ክፍሌ ቦልተና፣ ፍላጎት፣ ደጀኔ ሁንዴ፣ አዳነ ሁንዴ፣ ኢሳይያስ፣ ዮሐንስ ዘሚካኤል (ኤርትራዊ)፣ ሚሐባ ( ይሄ ተጫዋች በተለያየ ጊዜ ሁለት ጊዜ ካይሮ እና ጣልያን ጠፍቷል።) ለስምንት ቀን ካይሮ ከተማ ላይ አስቸጋሪ፣ በጥባጭ ሆነው ቆይተዋል። እንዲያውም የዐባይ ወንዝ የሚያልፍበት ድልድይ ላይ ይህ የሀገራችን ወንዝ ነው ማንም በዚህ አያልፍም መብታችን ነው በማለት አስራ አምስቱም መሬት ተኝተው መንገድ ዘግተው ይበጠብጡ ነበር። ፖሊስም አስራ አራቱን እጃቸውን አቆራኝቶ አስሮ ሲወስዳቸው አስራ አስተኛው ተስፋዬ ኡርጌቾ ትርፍ መጥቶ ከኃላቸው ይከተላቸው ነበር። የደርግ መንግስት ከግብፅ መንግስት ጋር ጥሩ ግኑኝነት ፈጥሮ እንዲመለሱ በመነጋገር በፖሊስ ተይዘው ወደ ውጭ ሀገር እንወሰዳችኋለን በማለት ለአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ሁለት መቶ ፖሊስ ተመድቦ በዋናው ኤርፖርት መግቢያ ሳይሆን ሰው እንዳያያቸው በጀርባ ሲወስዷቸው “ለምን?”.. ” አዲስ አበባ ከገባን እንገደላለን” ብለው በመፍራት ለአምስት ሰዓታት ያህል ከፖሊስ ጋር ሲደባደቡ ቆይተው ንብረታቸው ተዘርፎ ቆስለው እና ተፈንክተው እርቃናቸውን በአየር መንገዱ ፎጣ ብቻ ሰውነታቸውን ሸፍነው በልዩ አውሮፕላን አዲስ አበባ ገብተዋል። የደርግ መንግስትም በዓለም ሚዲያ ስም አጥፍተዋል በሚል እንዲረሸኑ (እንዲገደሉ) ትዕዛዝ ተላልፎ ወደ ከርቸሌ እስር ቤት ገብተዋል። በእስርቤት ለቀናት ቆይተው እንደ አጋጣሚ ሆኖ 1983 ግንቦት ወር ጦርነቱ ወደ መሐል ሀገር እየተቃረበ እና የደርግ መንግስት እየተበታተነ ሲመጣ ግንቦት ሰባት ቀን አስራ አምስቱ ተጫዋቾች ከእስር ቤት ወጥተዋል።

በዓመቱ 15 ተጫዋቾች ከሞት የተረፉንበትን ቀን በማሰብ “ግንቦት ሰባት የሚባል ማኀበር” አቋቁመው ተስፋዬ ኡርጌቾ የማኀበሩ ዋና ፀሐፊ አድርገውታል። በተለያዩ ምክንያቶች ተለያይተው ቀረ እንጂ እየተሰባሰቡ በየዓመቱ ያከብሩ ነበር። ከ29 ዓመት በኃላ ግን ግንቦት ወር እና የተስፋዬ ኡርጌቾ በድጋሚ ሲገናኙ ከዓመታት በፊት ያመለጠውን ሞት ሊያመልጠው አልቻለምና በአምስተኛው ቀን ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ