“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ከአቤል ያለው ጋር…

የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው የዘመናችን የዋክብት ገፅ የዛሬ እንግዳችን ነው። ወቅቱን በምን ሁኔታ እያሳለፈ እንደሚገኝ ከአዝናኝ ጥያቄዎች ጋር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።

አቤል ያለው የእግርኳስ ዕድገታቸው ፈጣን ከሆኑ ወጣት አጥቂዎች መካከል አንዱ ነው። በሐረር ሲቲ፣ ደደቢት፣ በመቀጠል በውሰት ወደ ፋሲል ከነማ ካመራ በኃላ በድጋሚ ወደ ደደቢት ተመልሶ ተጫውቷል። ከ2011 ጀምሮ ደግሞ አሁን በሚገኝበት ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወተ ይገኛል። ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እየተጠራ መጫወት የቻለው አቤል በኮከብ ደረጃ እና በዋንጫ የታጀበ ስኬት እስካሁን ባይኖረውም በግሉ ከሚያደርገው ጥረት እና መልካም እንቅስቃሴ አንፃር ወደፊት ብዙ ድሎች ያሳካል ተብሎ ይጠበቃል። የዘመናችን ከዋክብት የዛሬ ገፃችን ይህን ወጣት አጥቂ የተለያዩ አዝናኝ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሰጠንን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።

ጊዜውን የምታሳልፍበት ሁኔታ…?

ልምምዴን በሚገባ በጠዋት ተነስቼ እሰራለው። በቂ እረፍት ካደረኩ በኃላ። በተረፈ ፕሌይ እስቴሽን በመጫወት ቀሪውን ጊዜዬን አሳልፋለው

ጌም ታበዛለህ?

አዎ በጣም ነው የምወደው። ከእግርኳስ ውጭ የሚያዝናናኝ ፕሌይ እስቴሽን በመጫወት ነው።

ጨዋታ አስቀድመህ በህልምህ ጨርሰህ ታውቃለህ?

(እየሳቀ…) በክለብ ደረጃ መጫወት እንደጀመርኩ ሰሞን ለመጫወት ከሚኖር ጉጉት የተነሳ በጣም የምቸገርበት ነገር ነበር። አሁን ምንም አይነት ነገር ከጨዋታው አስቀድሞ በህልሜ ጨዋታ ጨርሼ አላውቅም።

የመጀመርያ ጎል?

በኢትዮጵያ ፕሪሚየምየር ሊግ መጫወት በጀመርኩ ጊዜ የመጀመርያ ጎሌ በውሰት ፋሲል ከነማ እያለው በ2009 አርባምንጭ ከነማ ላይ ያስቆጠርኩት ነው። አስታውሳለው ጨዋታው ከጀመረ ሁለት ደቂቃ አይሆነውም የመጀመርያ ጎሌን ሳስቆጥር።

በኬንያ አስተናጋጅነት በተደረገው በሴካፋ ዋንጫ ደቡብ ሱዳን ላይ በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎል ያስቆጠርኩት በብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ጎሌ ነው። ከዚህ ውጭ በቻን፣ በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ እስካሁን ለብሔራዊ ቡድን ጎል አላስቆጠርኩም።

ኳስ ተጫዋች ባትሆን..?

(እየሳቀ…) ኧረ አስቤውም አላቅም። እኔንጃ… ኳስ ተጫዋች ባልሆን ይሄን እሆናለው ብዬ አስቤ አላውቅም።

ማን ያዝናናሀል?

ከተጫዋች ከሆነ ሄኖክ አዱኛ (ሀላባ) ነው። ስታየው ዝምተኛ የማይናገር ይመስልሀል እንጂ ሀይለኛ ቀልደኛ ነው። ከእርሱ ጋር ከሆንኩ በጣም ነው የምዝናናው።

ከምግብ..?

ምግብ አልመርጥም፤ ያገኘሁትን እመገባለሁ። ግን ፓስታ በጣም እወዳለው።

የፍጥነትህ ምንጭ…?

(እየሳቀ..) ከምግብም፣ ከልምምድም የመጣ አይደለም። በተፈጥሮ ያገኘሁት ነው። ከድሮም ጀምሮ ቀጭን ፈጣን ነበርኩ።

አብሮህ ቢጫወት የምትመኘው?

አብሮኝ ቢጫወት ደስ የሚለኝ የኢትዮጵያ ቡናው አንበል አማኑኤል ዮሐንስ ነው። ምክንያቱም ለአጥቂዎች የሚመች ኳስን ስለሚያቀብል፤ እንዲሁም አቅልሎ ዘና አድርጎ ስለሚጫወት በጣም ይመቸኛል። ለዚህ ነው ከእርሱ ጋር ብጫወት ደስ የሚለኝ።

የሚያስቸግርህ ተጫዋች?

ብዙም የለም። ግን ምንም እንኳን አብሮኝ የሚጫወት ቢሆንም በልምምድ ወቅት በጣም የሚያስቸግረኝ አስቻለው ታመነ ነው። አስቻለው ኳሱን በሚገባ ያውቀዋል፣ ይችላል። ቶሎ በቀላሉ የማትሸውደው በጣም ምርጥ ተከላካይ ነው።

ወደ ውጭ ሀገር…

የተለያዩ እድሎች አሉ። ግን አሁን እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ከዚህ በፊት የተለያዩ እድሎች አሉ ተብሎ የቀሩ አሉ። ስለዚህ እስካሁን የተጨበጠ ነገር የለም። ሆኖም ዕድሉ ሲገኝ እንደማንኛውም ተጫዋች ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ህልሙ አለኝ።

ኮንትራትህ ተጠናቋል…

አዎ ተጠናቋል። ግን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አብሬ እቆያለው። ለቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማስገኘት እፈልጋለው። ዘንድሮ ዋንጫውን ማንሳት የሚያስችል ጥሩ ጥምረት እና አሪፍ ቡድን ነበረን። ያው የወቅቱ በሽታ ሊጉ ተሰረዘ እንጂ። በቀጣይ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ብዙ ስኬት ማጣጣም እፈልጋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ