ይህን ያውቁ ኖራል? ፲፪ | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ኮከቦች…

ዕለተ ሀሙስ በምናቀርበው “ይህን ያውቁ ኖራል?” አምዳችን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከቦችን የተመለከቱ ዕውነታዎችን በተከታታይ ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬም በሊጉ እና ኮከቦች ዙርያ ያሉ ዕውነታዎችን በክፍል 12 ጥንቅራችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለበርካታ ጊዜያት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ሽልማት የወሰደው ተጫዋች ታፈሰ ተስፋዬ ነው። ታፈሰ በ1996 በመብራት ኃይል (በጋራ)፣ በ1998፣ 2001 እና 2002 ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም 2008 ላይ በአዳማ ከተማ ባስቆጠራቸው ጎሎች የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ከዚህ መነሻነት ተጫዋቹ በድምሩ ለ5 ጊዜያት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ለበርካታ ጊዜያት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን ሪከርድ ይዟል።

– በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎሎችን አስቆጥሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው። በሦስት የተለያዩ ዓመታት ይህንን ክብር ያገኘው ጌታነህ 2009 ላይ በዮርዳኖስ ዓባይ (24) የተያዘውን በርካታ ግቦች አስቆጥሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የመሆንን ሪከርድ በአንድ ጎል (25) አሻሽሎ ተረክቧል።

– በተቃራኒው በአንድ የውድድር ዘመን ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ ያነሱ የሊግ ጎሎችን አስቆጥሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ተጫዋች ሐሰን በሽር ነው። በ1990 በተደረደው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ድንቅ ጊዜን ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያሳለፈው ሐሰን በጊዜው 9 ግቦችን አስቆጥሮ ነበር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው። (በወቅቱ የሊጉ ጨዋታዎች ብዛት 14 ብቻ እንደነበር ልብ ይሏል)

– በርካታ ተጫዋቾች በጣምራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው ያጠናቀቁበት ዓመት 1995 ላይ ነው። በዚህ የውድድር ዓመት ታፈሰ ተስፋዬ፣ መሳይ ተፈሪ፣ አህመድ ጁንዲ እና ቢኒያም አሰፋ እኩል 13 ጎሎችን አስቆጥረው በጣምራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው አጠናቀዋል።

– በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ነገር ግን አሁን ላይ በህይወት የማይገኘው ተጫዋች በረከት ሃጎስ ነው። በ1991 በሃዋሳ ከተማ ማሊያ 10 ጎሎችን አስቆጥሮ የውድድር ዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያገባደደው ተጫዋቹ ከሦስት ዓመታት በኋላ (1994) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ከአጥቂ መስመር ተጫዋች ውጪ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ተጫዋች የለም።

– ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ተጫዋች ዮርዳኖስ ዓባይ ነው። ዮርዳኖስ በ1993 እና 1994 በመብራት ኃይል እንዲሁም በ1995 በግማሽ ዓመት በመብራት ሃይል እና ኢትዮጵያ ቡና ባስቆጠራቸው ጎሎች ለ3 ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ግን አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።

– የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን ክብር ከአንድ በላይ ተጫዋቾች የተጋሩበት አጋጣሚ ለአራት ጊዜያት ተከስቷል። እነርሱም በ1991 (በረከት ሃጎስ እና አሸናፊ ሲሳይ) ፣ በ1995 (አህመድ ጁንዲ እና ዮርዳኖስ ዓባይ)፣ በ1996 ( ታፈሰ ተስፋዬ፣ መሳይ ተፈሪ፣ አህመድ ጁንዲ እና ቢኒያም አሰፋ) እና በ2003 (ጌታነህ ከበደ እና አዳነ ግርማ) ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!