የዳኞች ገፅ | ቀዳሚዋ ኢንተርናሽናል ሴት የመሐል ዳኛ ጽጌ ሲሳይ

ብዙ እልህ አስጨራሽ ተስፋ የሚያስቆርጡ ውጣ ውረዶችን በፅናት አልፋለች። በሀገር ውስጥ እና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ሀገሯን በመወል አገልግላለች። በርካታ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ከማጫወቷ በተጨማሪ የወንዶች ፕሪምየር ሊግን በመሐል ዳኝነት ማጫወት የቻለች የመጀመርያዋ ሴት ዳኛ ያደርጋታል። ሃያ ሁለት ዓመታት በቆየው የዳኝነት ህይወቷ ዙርያ በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ የአሁኗ የጨዋታ ታዛቢ ከሆነችው ጽጌ ሲሳይ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!

በኢትዮጵያ እግርኳስ ሴት ዳኞች ምንም ባልነበረበት ማለት ይቻላል፤ አንቺ ምን ምክንያት ወይም መነሻ ሆኖሽ ነው ዳኛ ለመሆን የተነሳሳሽው?

በመጀመርያ ዳኛ ከመሆኔ በፊት ለመብራት ኃይል ክለብ ለስምንት ዓመታት ሯጭ በመሆን ሰርቻለው። በልምምድ ወቅት ንፋስ መቶኝ በጣም በመታመሜ ምክንያት ሯጭ መሆን አቆምኩኝ። ከዛ በኃላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ዳግማዊ ምኒሊክ እየተማርኩ የቀድሞ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሰርካለም ከበደ ጋር እንተዋወቅ ነበር። እርሷም የተለያዩ ስፖርቶችን ትሞክር ስለነበር በተለያዩ አጋጣሚዎች እንገናኝ ነበር። ሰርካለም የዳኝነት ስልጠና ወስዳ አለማለፏን ነግራኝ ለምን አንቺ ስልጠናውን አትወስጂም አለችኝ። እኔ ደግሞ ዳኛ የመሆን ፍላጎቱ ስለሌለኝ እና እግርኳስን ስለማልወድ ብዙም አልተቀበልኳትም።

እግርኳስን ለምን ጠላሽ? ምክንያትሽስ ምንድነው ?

ምክንያቴ በህመም ነው ሩጫን ያቆምኩት። ተመልሼ ሲሻለኝ ወደ ሩጫው እገባለው ብዬ አስብ ስለነበር ሰርካለም ስትነግረኝ ለጊዜው አልተቀበልኳትም። እግርኳስን ፍፁም ጠልቼ አይደለም። በሩጫው ረጅም ርቀት እሄዳለው ብዬ አስቤ ስለነበረ ፍላጎቴ ያደላ የነበረው ሯጭ ለመሆን ነው።

ታዲያ እንዴት ወደ ዳኝነቱ ገባሽ ?

በቃ ሰርካለም ባገኘችኝ ቁጥር ኮርሱን እንድወስድ ታበረታታኝ፣ ትቀሰቅሰኝ ጀመር። አንድ ቀን እሺ ብዬ በ1988 ይመስለኛል የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስን ወሰድኩ። የመጀመርያው ስልጠናዬንም በጥሩ ብቃት አለፍኩ። ግን በዳኝነቱ ብዙም መቀጠል አልፈለኩም። ውስጤ የነበረው ተመልሼ ወደ ሩጫ እገባለው የሚል ስለነበር አልቀጠልኩበትም። ስልጠናውን ከወሰድኩ ከሦስት ዓመት በኃላ ጋሽ ኃይሉ ተሰማ፣ ጌታቸው ገብረማርያም፣ አቶ ከማል እስማኤል እና መኮንን አስረስ… በተለይ አብዛኛውን ጊዜ ኃይሉ ተሰማ ዳኛ እንድሆን በጣም ይፈልግ ነበር። የዛኔ ሰውነቴም ቀልጣፋ ስለነበር ወደ ዳኝነቱ እንዳመዝን ይፈልግ ነበር። እኔ ደግሞ ወደ ዳኝነቱ ለመግባት ፍላጎቱ አልነበረኝም። ያው በእነርሱ ኃይል እና ውትወታ በ1992 በመምርያ ዳኛ ጃን ሜዳ ማጫወት ጀመርኩ። የዛኔ የሴቶች ውድድር ብዙም ባይኖርም የቀበሌ፣ የትምህርት ቤቶች ፣ የፕሮጀክት ውድድሮች ነበሩ። እንዲሁም በየሰፈሩ የሚደረጉ ውድድሮች በራሳቸው ለዳኞች ብር እየከፈሉ የሚደረጉ ጨዋታዎች ለምሳሌ ቄራ ፣ ልደታ (ጨፌ ሜዳ) ሠፈሮች ሌሎችም አካባቢዎች የነበሩ ጨዋታዎችን አጫውተን። እንደገና የ ሲ፣ የ ቢ ቡድን ጨዋታዎች አሉ በቃ ጠዋት ወጥተን እዛው ክበብ እየፈለግን እየበላን ውለን ማታ ከቤት ተፈልጌ የምገባበት አጋጣሚ ነበር።

ፌዴራል ዳኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ ፈጅቶብሻል?

አይ ብዙ አልቆየሁም። ምክንያቱም ሴት ዳኛ ብዙ ስላልነበር እና ሰውነቴ በወቅቱ ከሩጫ ስለመጣው ቀልጣፋ በመሆኔ ፌደራል ዳኛ ለመሆን ብዙም አልተቸገርኩም። ወድያውኑ ማለት ይቻላል በ1994 ፌደራል ዳኛ ሆኛለው። ለአንድ ዓመት ረዳት ዳኛ ሆኜ ከሰራው በኃላ ዳኝነትን እስካቆምኩበት ጊዜ ድረስ በመሐል ዳኝነት ወደ 15 ዓመት አካባቢ አገልግያለው።

ሯጭ ሆነሽ ወደ ዳኝነቱ በመግባትሽ ጥሩ የዳኝነት ዘመን እንዲኖርሽ የረዳሽ ነገር አለ ማለት ነው ?

በጣም የሚገርምህ የዳኝነት የአካል ብቃት ፈተና ስፈተን አስቀድሜ ልምምድ ለማድረግ ስዘጋጅ ከዳኞች ጋር አልነበረም የምሮጠው፤ ከአትሌቶች ጋር እንጂ። ፈተና ደረሰ ሲባል እኔ ምንም የምጨነቅበት ነገር የለም። እስካሁን ድረስ ሰውነቴ በጣም ቀልጣፋ ነው። ስለዚህ ሯጭ ሆኜ ወደ ዳኝነቱ መግባቴ በጣም ጠቅሞኛል። ብዙ ሳልለፋ በተፈጥሮ በተሰጠኝ ፀጋ አገልግያለው።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመሐልም፣ በረዳትም ዳኝነት ያጫወትሽ የመጀመርያ ሴት ዳኛ ነሽ። እስቲ ይሄን አጫውቺኝ ?

አዎ። ዓመተ ምህረቱን አሁን ባላስታውሰውም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኒያላ ክንዴ ኃይሉ ዋና ዳኛ ሆኖ እኔ የእርሱ ረዳት ዳኛ ሆኜ የመጀመርያ ትልቅ ጨዋታ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ማጫወት ጀመርኩ። ከኔ ጋር አብራ ሰርካለም ከበደ ነበረች። እርሷ በረዳት ዳኝነቱ ስትቀጥል እኔ ወደ ዋና ዳኝነት በመግባት ማጫወት ጀመርኩ። ዋና ዳኛ በመሆን የፕሪምየር ሊግን ጨዋታ ያጫወትኩ የመጀመርያዋ ሴት ዳኛ በመሆን ስሜን ፅፌያለው። ከኔ በኋላ ነው ሌሎች የመጡት። የመጀመርያዋ በመሆኔም በጣም ደሰተኛ ነኝ።

በኢትዮጵያ ሴት ዳኞች ታሪክ በመሐል ዋና ኢንተርናሽና ዳኝነት የመጀመርያዋ ሴት ዳኛም ነሽ። ይሄም አንቺን ልዩ ያደርግሻል። በዚህ ላይ ያለሽ አስተያየት ምንድን ነው ?

ልክ ነው አብራኝ ሰርካለም ከበደ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ በመሆን አለች እንጂ ከዚህ በፊት ሴት ኢንተርናሽናል ዳኛ አልነበረም። እኛ የመጀመርያዎቹ ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች ነበርን። ከእኛ በኃላ ነው እነ ሊዲያ ታፈሰ፣ እነ ሳራ የመጡት። በዚህ መልኩ በኢንተርናሽናል ዳኝነቱ የመጀመርያ እንሁን እንጂ ዳኝነትን በሴት በመጀመር የመጀመርያዋ ሴት ዳኛ ቅድስት የምትባል ልጅ ነበረች። በጣም አሟት ብዙም ሳትቀጥል አቆመች። አሟት ፀበል ገብታ እየሄድኩ እጠይቃት ነበር። በኃላ አድራሻዋን አጥፍታ ማግኘት አልቻልኩም። ቅድስት በጣም ጎበዝ ደስ የምትል አርዓያ የምትሆን ዳኛ ነበረች።

ከአንቺ በፊት ኢንተርናሽናል ዳኛ አልነበረም። አንቺ ነሽ የመጀመርያዋ የመሐል ዳኛ የሆንሽው። በወቅቱ ይሄ ሲሆን ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብሽ ?

ኡ! በጣም ትልቅ ደስታ የሚፈጥር ስሜት ነው። ያው ስልህ ኢንተርናሽናል ሆኜ መሐል ገብቼ ሳጫውት ልነግርህ የማልችለው ትልቅ ስሜት ነበረኝ። የሚሰጥህ ክብር፣ የተጫዋቾች አክብሮት፣ ህዝቡ ጋር ያለው አቀባበል በጣም ደስ የሚል ነበር። ሜዳ ላይም ሳጫውት በጣም ኮስተር ብዬ ነበር የማጫውተው። ስለእኔ አላወራም ሰዉ በጣም ቢመሰክር ጥሩ ነው። እኔ ብዙም መናገር አልፈልግም። ብቻ ከፍተኛ ደስታ ነበረው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነሽ ከሀገር ውጭ ምን ምን ጨዋታዎችን አጫውተሻል። የሴቶች የአፍሪካ እና የዓለም ዋንጫ አጫውተሻል ?

የሴቶች የአፍሪካም ሆነ የዓለም ዋንጫም አላጫወትኩም። ምን ሆነ መሰለህ እዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ኤሊት ውስጥ ገብቼ አልፌ ካሜሩን የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለማጫወት በጊዜው ትርሀስ ረዳቴ ሆና እኔ ዋና ሆኜ ሄጄ እንደማጫውት ነበር የማውቀው። ከኔ ጋር የተፈተነችው ሊዲያ እዚህ ፈተና ላይ ወድቃ ነበር። የፊፋ ተወካይ የነበረው ካርሎስም ነበር። በቃ እኔ አልፌያለው እርሷ ወድቃለች ካሜሮን እንደምሄድ እርግጠኛ ሆኜ ስሜ እስኪመጣ ነበር የምጠብቀው። ሆኖም ሊዲያ ደቡብ አፍሪካ ሄዳ ኢንተርናሽናል ለመሆን ተፈትና አልፋ የአፍሪካ ዋንጫም ተመድባ መጣችና እኔ እንድቀር ተደርጎ እርሷ ተመደበች። ያው ምን ታደርገዋለህ ለማንስ ትናገረዋለህ በጣም ስሜቴ ተጎዳ። በጊዜው አንድ ሁለት ጋዜጠኞች ይህን መረጃ እናወጣዋለን ብለው ነበር። የዛን ጊዜ አቶ ግዛቴ እና ጥርወርቅ ነበሩ ኮሚቴ ውስጥ። ጋዜጠኞቹ እነርሱን ሊጠይቋቸው ሄዱ። ምን ምላሽ እንደሰጡ ግን አላቅም። እኔን ሲጠይቁኝ መናገር አልፈልግም ብዬ ዝም አልኩ። ያው እኔ መሄድ ሲኖርብኝ እርሷ ሄደች። ብቻ በጊዜው በሆነው ነገር አዝኜ ተቀመጥኩ።

መቼም አፍሪካ ዋንጫ አጫውታለው መስፈርቱን ሁሉ አሟልቻለው ብለሽ ስትቀሪ በጣም የምትቆጪበት አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለው?

በጣም! እንዳውም ዳኝነትን አቆማለው ብዬ ወስኜ ትቼ ሁሉ ነበር። ግን ጌታቸው ገብረማርያም፣ ይግዛው ብዙ፣ ኃይሉ ተሰማ፣ መኮንን አስረስ (ነፍሳቸውን ይማር) ከማል እስማኤል ቤቴ ድረስ መጥተው “ተሸንፈሽ ዳኝነትን መተው የለብሽም ለምን” ብለው ቀስቅሰው መክረውኝ እንደገና ከተውኩት ከዓመታት በኃላ በ2003 ወደ ዳኝነት እንደገና ተመልሻለው። ዳኝነትን ማቆም ከነበረበኝ የዛን ዘመን ነበር። በጣም የሚቆጨኝ ሰዓት ነበር። ምን ታደርገዋለህ ፈጣሪ መልካም ነው። ይገርምሀል በዚህ ብስጭት ሜዳ ላይ እርሱን እያሰብኩ አንድ ተጫዋች ተንሸራቶ ቁርጭምጭሚቴን መቶኝ ተሰንጥቆ ለአንድ ዓመት በጉዳት እርቄ ነበር። ሰውነቴም በጣም ወፍሮ ነበር። ግን ጠንክሬ ጠዋት እና ማታ ጫካ ገብቼ ሠርቼ የሰውነቴን ኪሎ አስተካክዬ በድጋሚ ፈተናውን አልፌ ወደ ኢንተርናሽናል ማዕረጌ ተመልሻለው።

አንዳንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ዳኝነት የተግባርም የፁሑፍም ፈተና አልፈው ሆኖም የመጎተት አልያም ሌሎች ሴራዎች አሉ ይባላል። ይህ የኢትዮጵያ የዳኝነትን እድገትን ጎድቶታል ትያለሽ ?

በጣም እንጂ! አቅሙ ኖሮህ ችሎታውን ይዘህ እዛው ነው ተደብቀህ የምትቀረው ወይም የምትቀመጠው። እንግዲህ ምን ታደርገዋለህ ወደፊት ይስተካከላል። አሁን በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር እና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ውስጥ ገብቻለው። ወደፊት ሴቶች በአቅማቸው እና በችሎታቸው ወደ ኃላ እንዳይቀሩ ለማብቃት እና እንዲህ ያለህ ክፍተት እና ችግር እንዳይፈጠር በመነጋገር ሊፈታ ከቻለ እሞክራለው። የተወሰነ እንቅስቃሴ እያደረግኩ ነው። የኮሮና በሽታ መጥቶ ተቋረጠ እንዳንገፋበት ሆነ እንጂ በቀጣይ የምሰራው ነው።

ሴት ሆኖ ዳኝነት በራሱ በጣም ከባድ ነው። በተፈጥሮም የሚመጡ ፈተናዎች አሉት። ለአንቺ ይሄን ያህል ዓመት በጥንካሬ ለመዝለቅሽ ምንድነው ምክንያቴ ትያለሽ ?

የራስህ ጥንካሬ፣ በልምምድ ጊዜ በአግባቡ መስራት፣ የሚሰጥህን ትምህርቶች በሚገባ መከታተል፣ በየጊዜው ተሻሽለው የሚወጡ የፊፋ ሕጎችን በሚገባ በማየት፣ ሜዳ ላይ ያለህን ሥራ እያጠናከርክ መሥራቱ ጠቅሞኛል። እንዲሁም ለኔ አስቀድሞም በስፖርት ያለፈ ሰውነት በመያዜ ብዙም የሜዳ ላይ ፍርሀት አልነበረኝም። ፈጣሪ ይመሰገን በሄድኩበት ጨዋታ ሁሉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የቡድኖቹ አመራሮች በኔ ደስተኛ ሆነው ነው ዳኝነትን ያቆምኩት። በኔ በዳኝነት ዘመኔ ይሄን ሁሉ ጨዋታ ሳጫውት አንድ ቀንም ሜዳ ላይ ጨዋታ ተረብሾብኝ አያቅም። ትልቅ ጨዋታዎችን አጫውቻለው። በወንዶች ፕሪምየር ሊግ እንደ ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ ዓይነት በጣም ውጥረት ያለባቸው የሚፈሩ ጨዋታዎችን በጥንቃቄ ከወንድ ረዳት ዳኞች ጋር አጫውቻለው። ሴት ዋና ዳኛ ወንድ ረዳት ዳኛ ተመድቦላት ስታጫውት አስበኸዋል? ይህ ትልቅ ጥንካሬ፤ የነበረኝን በራስ መተማመን የሚያሳይ ነው።

በዳኝነት ዘመንሽ ያገኘሻቸው የኮከብነት ሽልማቶች አሉ

በ2007 እና 2009 ላይ በሴቶች የምስጉን ዳኝነት ክብርን አግኝቻለው። ከዚህ ውጭ የተለያዩ የምስጋና ሽልማቶችን አግኝቻለው።

በዳኝነት ዘመንሽ መቼም የማትረሽው ገጠምኝ ካለሽ ንገሪኝ። አስቂኝም አሳዛኝም ቢሆን ?

ብዙም ገጠመኝ የለኝም። አንድ ሁለቱን ግን ልንገርህ። ባህር ዳር ላይ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የብሔራዊ ሊግ ጨዋታ ነበር። ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ፖሊስ ሲጫወቱ ጨዋታው ካለቀ በኃላ ከሜዳው እየወጣው የተሸነፈው ቡድን የዩኒቨርሲቲ አንድ ደጋፊ መጥቶ ‘ቤትሽ አርፈሽ ተቀምጠሽ፣ ዝም ብለሽ ለባልሽ ወጥ አትሰሪም? እዚህ ሜዳ ላይ ትዘያለሽ አይደል? ባለጌ’ ብሎ አንድ ደጋፊ የተናገረኝን መቼም አልረሳውም (እየሳቀች)። ሌላው ሜዳ ውስጥ ያዘንኩበት ደግሞ አዲስ አበባ ስታድየም ባንክ ከ ሀዋሳ እየተጫወቱ የባንኩ መስፍን አሕመድ (ጢቃሶ) ፋውል ይሰራና ኳሱ ለተቃራኒ ቡድን ይደረሰዋል። እኔ ደግሞ አድቫንቴጅ ብዬ ጨዋታው እንዲቀጥል አደረኩ። ግን መስፍን ሲወድቅ እጁ ዞሯል ለካ እየሄድኩ ወይኔ እናቴ እያለ ሲያለቅስ፣ ሲጮህ ሰምቼ ዞር ስለ ወድቋል። ጨዋታውን አስቁሜ ወደ መስፍን ስሔድ ያየሁት ነገር በጣም ስሜት የሚረብሽ ነበር። እጁ ዞሯል እያለቀስኩ ይስሐቅ ሽፈራው እና ዶ/አያሌው እየሮጡ መጥተው የወለቀ እጁን ወደ ነበረበት መለሱት እኔ መልበሻ ክፍል ገብቼ በጣም ነው ያለቀስኩት። ከዛ በኃላ ጨዋታውን እንዴት እንዳጫወትኩኝ አላቀውም። እስከ ዛሬም ድረስ ሳስታውሰው ውስጤን ይረብሸዋል።

ዳኝነትን መቼ አቆምሽ? አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለሽ?

2010 መጨረሻ ላይ ዳኝነትን አቁሜያለው። አሁን ስልጠና ወስጄ የጨዋታ ታዛቢ (ኮሚሽነር) በመሆን እየሰራሁ ነው። በቅርቡም በሴቶች ሊግ የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ውስጥ ገብቼ እያገለገልኩ እገኛለው።

በመጨረሻ…

ዳኝነት ለኔ ብዙ ሰው ያወኩበት፣ የተለያዩ ሀገሮች የዞርኩበት ብዙ ጨዋታዎችን ያጫወትኩበት ለኔ ዳኝነት ብዙ ነገሬ ነው። በጣም የምወደው ሙያ ነው። በአህጉር አቀፍ ውድድር ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚያስችል አቅሙም፣ ብቃቱ ነበረኝ። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ከኔ አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ህልሞቼ ተጨናግፏል። በዚህ ሁሌም ብከፋም ወደፊት በርካታ ሴት ዳኞች ሀገሬን ወክለው እንዲወጡ በምችለው መጠን አግዛለው። በኔ ጊዜ ተያይዘን ነበር ለማጫወት ወደ ተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የምንወጣው። እኔ ካለው ሳራ እና ሰርኪ አሉ እነርሱ ሲወጡ ተስፋነሽ እና ትርሀስ ነበሩ። እነርሱም ሲያቆሙ ወይንሸት እና ወጋየሁን ይዤ በረዳትነት እንወጣ ነበር። አሁን ይሄ የለም ቆሟል። በጣት የሚቆጠሩ ኢንተርናሽናል ሴት ዳኞች አሉ። ሆኖም ለጨዋታ በተደጋጋሚ ሲወጡ አልመለከትም። ይህ መስተካከል አለበት። በተረፈ ያው ብዙ ነገሮችን አላስታወስኩም እንጂ ታሪኬ ሰፊ ነው። እናተም አክብራቹ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለው። ሴት ዳኞቻችን በርቱ ጠንክሩ ብዙ ፈተናዎች ይኖራሉ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም እላለው።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!