ፊፋ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ውሳኔ አስተላለፈ

በጋናዊው የቀድሞው ተጫዋቹ ሚካኤል አኩፉ የተከሰሰው ድሬዳዋ ከተማ ለተጫዋቾቹ የደሞዝ እና ካሳ ክፍያ ተፈጻሚ እንዲያደርግ በፊፋ ውሳኔ ተሰጠበት፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያልተሳካ ቆይታ ከነበራቸው የውጪ ሀገር ዜጋ ተጫዋቾች መካከል የ33 ዓመቱ ጋናዊ ዜግነት ያለው ሚካኤል አኩፉ ተጠቃሽ ተጫዋች ነው፡፡ የሊባኖሱን ክለብ አል አንሳርን ከለቀቀ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ መቶ መቐለ 70 እንደርታን 2009 በመቀላቀል የአንድ ዓመት ቆይታን ካደረገ በኃላ 2010 ላይ ወደ ድሬዳዋ ያመራው፡ ተጫዋቹ በዛው ዓመት በድሬዳዋ የመጀመሪያውን ዙር በመጫወት ካሳለፈ በኃላ ወደ ሀገሩ ለእረፍት አምርቶ ለሁለተኛው ዙር ወደ ድሬዳዋ ለመመለስ በመጠበቅ ላይ እያለ ክለቡ የአየር ትኬት እንደማይልክና የአራት ወር ደመወዝ ስለተከፈለለው እንደማይፈልጉት መልስ እንደተሰጠው ይናገራል፡፡ በወቅቱ ተጫዋቹ ለአንድ ዓመት ለድሬዳዋ ለመጫወት ፈርሞ የአራት ወር ደመወዝ ቢያገኝም ቀሪ የስምንት ወር ውል እያለው በክለቡ ለመሰናበት ስለመገደዱ ክስ አቅርቧል፡፡

ፊፋም ጉዳዩን ሲመለከት ከቆየ በኋላ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ውሳኔን አስተላልፏል፡፡ ፊፋ በውሳኔው የተጫዋቹ ስንብት ተገቢ ያለመሆኑን ገልፆ ድሬዳዋ ያልከፈለው የስምንት ወር ደመወዝ ማለትም ስምንት መቶ ሺህ ብር እንዲሁም የሞራል ካሳ ስድስት መቶ ሺህ ብር ተጨምሮ በድምሩ 1.4 ሚሊዮን ብር እንዲከፍለው በማለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስፈፅምለት ዘንድ በኢሜል መላኩን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በአስራ አራት ቀናቶች ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ እና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለተጫዋቾቹ ገንዘቡን ከፍሎ ካላጠናቀቀ የእግድ ውሳኔ እንደሚተላለፍበትም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!