በሰንጠረዡ ላይኛው እና ታችኛው ባላቸው ፉክክር እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ፍለጋ የሚፈለሙት ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በሰላሣ ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ቀጥረው ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ምዓም አናብስት ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው በተከታታይ ሁለት መርሐ-ግብሮች ነጥብ ተጋርተው መውጣት ቢችሉም ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በቂ አልሆነላቸውም። ቡድኑ ትልቅ ትርጉም በነበራቸው እና ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራቱ እንዲሁም አዳማ ከተማ በመጨረሻው ሳምንት ድል አድርጎ የነጥብ ልዩነቱን ማጥበቡን ተከትሎ ያለበትን ደረጃ አስጊ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት መሪው መድንን በሚገጥበት የነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ነጥብ እያስመዘገበ መዝለቅ ግድ ይለዋል።
ከድል ጋር ከተራራቀ አራት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ በነገው ተጠባቂ ጨዋታ በርከት ባሉ ጉዳዮች መሻሻል ይጠበቅበታል፤ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ማስተካከልም የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ትልቁ ስራ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ተጋጣሚያቸው ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ያስቆጠረና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኝ እንደመሆኑም የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ እንደሚሆን እሙን ነው። ቡድኑ በነገው ዕለት በመከላከሉ ረገድ የሚያሳየው ብቃትም የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅም አለው።
ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ልዩነት መሪነቱ ላይ የተሰየሙት ኢትዮጵያ መድኖች ለዋንጫ የሚያደርጉት ጉዞ ለማፋጠን ድልን እያለሙ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
በባህርዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም በመጨረሻው መርሐ-ግብር ፋሲል ከነማን ሁለት ለባዶ ያሸነፉት መድኖች አሁን ያለው የመሪነት ልዩነት ባለበት ለማስቀጠል አልያም ለማስፋት ሁሉንም ጨዋታዎች በእኩል መመልከት አስፈላጊው በመሆኑ ከነገው ጨዋታም ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ያልማል። ከሌሎች የሊጉ ክለቦች በተለየ ወጥነት ያለው ብቃት በማሳየታት እዚህ የደረሱት መድኖች በተለይም በአዳማ እና ሀዋሳ ቆይታቸው በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ አልጣሉም በተጨማሪም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ቀዳሚ መርሐ-ግብር በወላይታ ድቻ በ28ኛው ሳምንት ደግሞ በባህርዳር ከተማ ከደረሱባቸው ሽንፈቶች በኋላ የሰጧቸው ፈጣን ምላሾቹ እንዲሁም በቅርብ ሳምንታት ያሳዩት ሁለንተናዊ ብቃት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምን ያህል ለውጤት የተሰራ ስብስብ እንደገነቡ ያሳየ ነበር። በነገው ዕለትም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ያዘነበው የአጥቂ ጥምረቱ ለተጋጣሚው ትልቅ ፈተና መሆኑ አይቀሪ ነው።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል አምበሉ ያሬድ ከበደ ከሕመሙ ባለማገገሙ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን እግድ ላይ የሚገኘው ያብስራ ተስፋዬም በጨዋታው አይሳተፍም። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በኢትዮጵያ መድን በኩል ከሚልዮን ሰለሞን በተጨማሪ መሐመድ አበራም በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ተጫዋች ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያ ዙር በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን አራት ለባዶ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።