በጠንካራ የመከላከል አቅማቸው ታግዘው ኢትዮጵያ ቡናዎች አዳማ ከተማዎችን 2-0 በመርታት የሊጉን መሪ መከተላቸውን ተያይዘውታል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ወላይታ ድቻ ላይ ድል ካደረገው ቡድናቸው ላይ አንድ ቅያሬዎችን ሲያደርጉ በዚህም አንተነህ ተፈራን በሚኪያስ ፀጋዬ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታው ቡድን ውስጥ በተመሳሳይ አንድ ተጫዋች ሲለውጡ አሜ መሐመድን በነቢል ኑሪ በማካተት ለጨዋታው ቀርበዋል።
ፌደራል ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በመሩት ይህ ጨዋታ ገና ከጀምሩ አንስቶ በሁለቱም በኩል ጎሎችን ለማስቆጠር ወደ ግብ ክልል የመድረስን ጥረት ተመልክተናል። በ6ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ዲቫይን ዋቹኩዋ ሳይጠበቅ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው እና ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ የወጣበት ከአንድ ደቂቃ በኋላ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ነቢል ኑሪ ከግራ መስመር አምልጦ ወደ ሳጥን በመግባት ያቀበለውን ቢንያም አይተን በማይታመን መልኩ ወደ ላይ የላካት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
ከቆሙ ኳሶች አደጋ በመፍጠሩ የተሻሉ የነበሩት ቡናማዎቹ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ራምኬል ጀምስ በግንባሩ በመግጨት ያደረገው አደገኛ ሙከራ ባይሳካለትም በድጋሚ በ22ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የማዕዘን ምት መምቻው አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ዲቫይን የመታውን ራምኬል ኳሷንበመምታት ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል አስገኝቷል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ባሉት አመዛኙ ደቂቃዎች ሙከራ አልባ እንቅስቃሴ ነበር። ቡናማዎቹ በኩል በኳስ ቅብብሎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ባይቸገሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ቢደርሱም
ጥቂት የማይባሉ ስህተቶችን እየሰሩ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ተስተውሏል።
ከዕረፍት ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ተመጣጣኝ በሆነ እንቅስቃሴ ቢቀጥልም ቡናማዎቹ በተሻለ ጎል በማስቆጠር መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ጎል በ59ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ኮንኮኒ ሃፍዝ በሦስት ተጫዋቾች መሐል ኳሱን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ወደ ጎል የሸረፈውን አማኑኤል አድማሱ መላኩ እና ፍቅሩን ኳሱን ለማራቅ ሲገባበዙ በፍጥነት ኳሱን ነጥቆ አምልጦ ወደ ፊት በመሄድ በተረጋጋ ሁኔታ ኳሷን ቺፕ አድድጎ ማራኪ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ሁለተኛው ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የወረዱት አዳማዎች እንቅስቃሴያቸው እየተቆራረጠ ሲቀጥል። ቡናማዎቹ በኩል በተለይ ሳይጠበቁ በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የሚያደርጓቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች ጨዋታውን ሳቢ አድርጎታል። በዚህም ሂደት ኢትዮጵያ ቡናዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ሊያድንበት ችሏል።
የጨዋታው መጠናቀቂያ አስራ አምስት ደቂቃዎች ለመነቃቃት የሞከሩት አዳማዎች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ቢታትሩም ከጥረት ባለፈ የማይቀመሰውን ጠንካራውን የቡናማዎቹን የመከላከል አጥር አልፈው አስደንጋጭ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረዋል። ኳስ ሲያጡ በህብረት እየተከላከሉ ኳስ ሲያገኙ ደግሞ በህብረት ወደ ፊት በመሄድ ያልተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሌላ ሙከራ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ አድርገው ግብጠባቂው ዳግም አሁንም ጎል እንዳይሆን ከልክሏቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከነበራቸው የበላይነት አንፃር የተገኙት አጋጣሚዎች ወደ ጎልነት ቢቀይሩ ኖሮ ምሽቱ ለአዳማ ከተማዎች ከዚህ በላይ አስከፊ ይሆን ነበር። ጨዋታው 2-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ቡናማዎቹ የሀዋሳ ቆይታቸውን በድል ማጠናቀቅ ችለዋል።