ሪፖርት | የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማን ነጥብ አጋርቷል

ሪፖርት | የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማን ነጥብ አጋርቷል

ሁለት ቀይ ካርዶችን ባስመለከተን በምሽቱ ጨዋታ አፄዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ ከ ሀይቆቹ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።


የ31ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ የመርሐግብሩ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከፋሲል ከነማ አገናኝቷል። ሀዋሳ ከተማዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 ካሸነፉበት የጨዋታ አሰላለፍ የጨዋታ አሰላለፍ ግብጠባቂውን ሰይድ ሃብታሙ ፣ ፈቃደስላሴ ደሳለኝ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ዳዊት ታደሰን በማሳረፍ በምትካቸው ፅዮን መርዕድ፣ ሰለሞን ወዴሳ፣ አማኑኤል ጎበና እና ማይክል ኦቱሉን ሲያስገቡ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ከንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ ዳንኤል ፍፁም እና ማርቲን ኪዛን በማስወጣት በምትካቸው ምኞት ከበደ እና ቢንያም ላንቃሞን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ምሽት 12:00 ሲል በዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በአሳቴዩ ስታዲየም የተጀመረው ይህ ጨዋታ ጅማሮው ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተቀራራቢ የሚባል የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረግ ረገድ በዓሊ ሱሌይማን እና በተባረክ ሔፋሞ አማካኝነት ሀዋሳ ከተማ ከተማዎች ቀዳሚ ነበሩ።

በሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የሆነ ብልጫ ቢኖራቸውም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ሀይቆቹ የተሻሉ ነበሩ። ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው በመቀባበል በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን 45ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ብሩክ ታደለ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ፋሲሎች በረጃጅም ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ወደ ግብ በመድረስ እና የግብ ዕድሎችን በማግኘት ረገድ ባሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ሙከራዎችኝ ሳያስመለክቱን ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ፋሲል ከነማወች 58ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የግራ መስመር ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው መልሶበታል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች በምኞት ከበደ አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ቢችሉም በዕለቱ መስመር ዳኛ አማካኝነት ግቡ ተሽሯል። ይሄም በፋሲላውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።

ሀዋሳ ከተማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከኋላው የሜዳ ክፍል በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን በማለፍ ድንቅ የሆነ ግብን በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ የቻለበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ፋሲል ከነማዎች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ በተጨማሪ ደቂቃዎች ሳጥን ውስጥ ጌታነህ ከበደ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጌታነህ ከበደ 90+5′ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን ከመሸነፍ የታደገ ግብ ማስቆጠር ችሏል።


በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በተፈጠረ ግርግር በፋሲል ከነማ በኩል ሀብታሙ ተከስተ እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ በፈጠሩት ሰጣገባ በዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ውሳኔ መሰረት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል።ይህንንም ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ 1-1 በመውጣት ነጥብ መጋራት ችለዋል።