የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አዲስ ክለብ ተቀላቅሏል

የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አዲስ ክለብ ተቀላቅሏል

ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው አጥቂ አዲስ ክለብ አግኝቷል።

ከአራት ዓመት በፊት ሀገራችን ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሀገሩን ኤርትራ በመወከል ባሳየው ጥሩ ብቃት ባህር ዳር ከተማን በመቀላቀል ራሱን ከሊጉ ጋር ያስተዋወቀው እና የባለፉትን ሁለት ዓመት በሀዋሳ ከተማ ሲያገለግል የቆየው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብፅ ማቅናቱን ማናጀሩ አዛርያ ተስፋፅዮን ነግሮናል።

ፈጣኑ አጥቂ ዓሊን ያስፈረመው የግብፁ ክለብ ኢስማሊያ ኤሌክትሪሲቲ ሲሆን ለሁለት ዓመት ለመጫወት የሚያስችለውን ፊርማውን አኑሯል። ኢስማሊያ ኤሌክትሪሲቲ ክለብ በ1935 እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር የተመሠረተ ሲሆን በያዝነው ዓመት ነው ከታችኛው ሁለተኛ የሊግ ውድድር ወደ ዋናው ሊግ በማደግ የቻለው። በግብፃዊው አሰልጣኝ ራይዳ ሸሀታን የሚመራው ቡድኑ የሊጉን የመጀመርያ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ ከኤል ጉና ጋር በመጫወት የሚጀምር ይሆናል።

ዓሊ ሱሌይማን በኢትዮጵያ ሊግ በነበረው ቆይታ ጥሩ የሚባል የውድድር ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን በ2016 እና 2017 ዓ/ም ለተከታታይ ሁለት ዓመት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቁም ይታወሳል።

አጥቂው ለሁለት ዓመታት የፈረመ ሲሆን በመጀመሪያው ዓመት 70,000 የአሜሪካን ዶላር በሁለተኛው ዓመት ደግሞ 80,000 የአሜሪካን ዶላር የሚከፈለው ይሆናል።