በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ 09፡00 ሲል በከፍተኛ ፉክክር ታጅቦ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፈው ባለፈው ሳምንት ግን በሮዱዋ ደርቢ የተሸነፉት ሐይቆቹ ይህ ሽንፈት ጥሩ አጀማመራቸው ላይ ውሃ የቸለሰ ነበር። ሆኖም ዛሬ በውጤት ማጣት ውስጥ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ ጋር የሚጫወተው ቡድኑ ከፍተኛ ፉክክር ማድረግ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ዋጋው ቀላል አይሆንም። በሮዱዋ ደርቢ ጉዳት አስተናግዶ ወጥቶ የነበረው ሰለሞን ወዴሳ ከጉዳቱ ማገገሙ ሲታወቅ የተቀሩት የቡድኑ አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ከካፍ ኮንፌዴሬሽን የድምር ውጤት ተሸናፊነት በኋላ ባደረጓቸው የሊጉ ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፉት ወላይታ ድቻዎች አጀማመራቸው ውጥረት የተሞላበት ሆኗል። በጨዋታዎቹ ምንም ጎል ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ ዛሬ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያለውን ሁሉ ሰጥቶ ነጥብ ማግኘት የማይችል ከሆነ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ሦስት ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዶ ውጥረቱን ራሱ ላይ የሚጨምርበት ፤ ነጥብ የሚያገኝ ከሆነ ደግሞ በቀጣይ ከሲዳማ ቡና ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ በራስ መተማመኑን በመጠኑ ከፍ የሚያደርግለት ይሆናል። መልካሙ ቦጋለ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፍ ብቸኛው የጦና ንቦቹ ተጫዋች ነው።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን ለ22 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ 8 ጊዜ ወላይታ ድቻ ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፈዋል። በሰባት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ሲለያዩ ፤ ሀዋሳ ከተማ ደግ 26 ግቦችን ወላይታ ድቻ ደግሞ 22 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
ነገሌ አርሲ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፉ የሚገኙትን ነጌሌዎችን ከ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው ጨዋታ 10፡00 ሲል በአ.አ ስታዲየም ይካሄዳል።
ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1ለ1 ተለያይተው ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 የተረቱት ነጌሌ አርሲዎች በመከላከሉ ረገድ እየሠሯቸው የሚገኟቸው ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሏቸው ይገኛሉ። ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድ ጠንካራ ቢሆንም ሙሉ ደቂቃዎችን ትኩረት ላይ አለመገኘቱ ከድል ጋር እንዳይታረቅ አድርጎታል። በተለይም ከቀኙ የማጥቃት ክፍላቸው የሚገኙ የግብ ዕድሎችን በተመሳሳይ በግራ መስመር ከሚነሱ ኳሶች መፍጠር እየቻለ ያልሆነው ቡድኑ ይህንን ክፍተት መፍጠርም ትልቅ መሻሻል እንደሚያስገኝለት እሙን ነው።
በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ የዓምናው ቻምፒዮን መድን ለካፍ ቻምፒዮንስ ውድድር ላይ በመሆኑ ጨዋታዎች የተራዘመባቸው ፈረሰኞቹ ከአዲስ አበባ ከተማ የሕዳሴ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ የ4ለ1 ሽንፈት በኋላ ከፍተኛ መሻሻል ዐሳይተው ቻምፒዮን ሲሆኑ ከዛ በኋላ በተደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ያሳዩት በራስ መተማመንም በደጋፊዎች ብዙ እንዲጠበቁ አድርገዋል። ቡድኑ በቢኒያም ፍቅሩ እና አቤል ያለው ላይ ጥገኛ እንዳይሆን ብዙ ስጋቶች መስተጋባት ቢጀምሩም በተለይም የተከላካይ መስመሩ ባሳለፍነው ሳምንት ያሳየው ንቃት ግን ትኩረትን የሚስብ ነበር።
በፈረሰኞቹ በኩል አዲሱ የግብ ዘብ ኬንያዊው ፋሩክ ሺካሎ ለዛሬው ጨዋታ መድረሱ ሲታወቅ የተቀሩ የቡድኑ አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በነጌሌ አርሲ በኩል የቡድን ዜና ማግኘት አልቻልንም።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ፋሲል ከነማ ከ ሲዳማ ቡና
ሁለቱ ከድል የተመለሱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው።
በመጀመሪያው ጨዋታ ከንግድ ባንክ ጋር 1ለ1 ተለያይተው ባሳለፍነው ሳምንት ግን ወልዋሎን 2ለ0 ያሸነፉት ፋሲል ከነማዎች በተለይም እነዚህ ከዕረፍት መልስ የተገኙ ግቦች የቡድኑ የማጥቃት አማራጭ የተሰጋውን ያህል ጠባብ እንዳልሆነ ሊያመላክቱ ይችላሉ። ቡድኑ በወቅታዊ ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘውን ሲዳማ ቡናን ማሸነፍ የሚሰጠው መነሳሳት ከፍተኛ በመሆኑ የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂነት ከፍ ያደርገዋል።

በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው ሊጉን በ100% የማሸነፍ ንጻሬ እየመሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ያሉበት ከፍተኛ በራስ የመተማመን ደረጃ እስከየት ያዘልቃቸዋል ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የዛሬው ጨዋታ በመጠኑም ቢሆን መልስ የሚሰጥ ይሆናል። በሮዱዋ ደርቢ ሀዋሳን በፍጹም ቅጣት ምት ጎል 1ለ0 ያሸነፉት ሲዳማዎች በመከላከሉ ረገድ ባሳለፍነው ሳምንት ተሻሽሎ የቀረበውን ፋሲልን ለመርታት የማጥቃት አማራጫቸውን እንደ መጀመሪያው ሳምንት ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
በዐፄዎቹ በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ሀብታሙ ተከስተ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በሲዳማ ቡና በኩል በወልዋሎው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የሮዱዋ ደርቢ ጨዋታ ያለፈው መስፍን ታፈሰ ለዛሬው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ሌሎቹ የቡድን አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
በሊጉ 16 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ፋሲል ከነማ ዘጠኝ ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል፤ ሁለት ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ፋሲል ከነማ 24 ግቦች ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና ደግሞ 17 አስቆጥሯል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

