እጅግ ከፍ ያለ ተጠባቂነት እና በወጣት የተገነቡ ስብስቦችን ማስታረቅ ከበድ ያለ ፈተና ይመስላል ፤ ሁለቱ የመዲናይቱ ቡድኖች ይህን ፈተና እንዴት ይወጡታል?
ሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሐግብር ላይ ደርሷል ፤ ታድያ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎች ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች መካከል በወጣቶች የተሞሉት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳይ አንዱ ነው።

እርግጥ ሁለቱ ቡድኖች በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ይበልጥ ወደ ዕድሜ እርከን ቡድኖቻቸው እና ከታችኞቹ የሊግ እርከኖች የሚገኙ ባለተሰጥኦዎችን መጠቀም የጀመሩት ዘንድሮ ባይሆንም ሊጉ ከዓመታት በኃላ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሱ ጋር ተያይዞ ይህ ጉዳይ ዳግም የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
ለሊጉ በዋና አሰልጣኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ጠርዝ እየተመለከትነው በሚገኘው አሰልጣኝ ዐብይ ካሳሁን የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአራት የሊግ ጨዋታዎች አራት ነጥብ መሰብሰብ ሲችሉ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ከሦስት ጨዋታዎች (አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው) ስድስት ነጥብ መሰብሰብ ችለዋል።
በነጥብ ረገድ ከመዘነው የሁለቱም ቡድኖች አጀማመር አስከፊ ባይመስልም በደጋፊዎች ዘንድ ካለው ከፍ ያለ የተጠባቂነት ስሜት(Expectation) አንፃር ከሚዛን በታች እንደሚሆን መገመት አያዳግትም ፤ ለዚህም ይመስላል ሁለቱም ቡድኖች ሽንፈት ባስተናገዱባቸው የመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎቻቸው በተጫዋቾች እና በአሰልጣኝ ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠሩ የተቃውሞ ድምፆችን ያደመጥነው።
በሁለቱም ፅንፍ የተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ድምፆች የደጋፊነት መሰረታዊ ባህሪያት ናቸው ፤ መደገፍ ትክክል መቃወምም ስህተት ነው የሚያስብል ብያኔ የሚያሰጥ ጉዳይ ባይኖርም ሁለቱም ፅንፎች ግን ከስሜት እና ከግላዊ መሻት ባለፈ አመክንዮ ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑ ይመረጣሉ።
ክለቦቹ ካላቸው የገዘፈ የቀደመ ታሪክ መነሻነት በደጋፊዎች ዘንድ የሁልጊዜም ማነፃፀሪያቸው የትላንት ከፍታ መሆኑ ትክክል ቢሆንም ክለቦቹ አሁን ላይ ያሉበትን ሁኔታ ግን መገንዘብ ተገቢ ይመስላል ፤ ምክንያቶቹን ወደ ጎን ትተን የክለቦቹን ወቅታዊ የፋይናንስ ቁመና ለመፈተሽ ለሞከረ ሁለቱ ክለቦች በቀደመው ጊዜ በአንፃራዊነት በሌሎች ክለቦች ላይ የነበራቸው የፋይናንስ የበላይነት አሁን አብሯቸው አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።

ታዲያ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ላስገባ እና አሁን ላይ ሁለቱ ቡድኖች በስብስባቸው የያዟቸውን የተጫዋቾች ጥራት ደረጃ ላስተዋለ ሁለቱም ቡድኖች ከቀደሙት አመታት አንፃር ከደጋፊዎቻቸው የሚጠብቁት ነገር የበዛ ስለመሆኑ መገመት አያስቸግርም ፤ ሁለቱም ቡድኖች አመዛኙ ስብስባቸው በሊጉ ከአንድ ዓመት የዘለለ የመጫወት ልምድ በሌላቸው ወጣቶች የተገነቡ እንደመሆናቸው ደጋፊዎች ለእነዚህ ተጫዋቾች ደጀን እንዲሆኑ ይጠበቃል።
ወጣት ተጫዋቾች ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው ወደ ሚጠቀሙበት ደረጃ ለማድረስ ረዘም ያለ ሂደትን እንደሚወስድ ይታወቃል ፤ ታዲያ በዚህ ውስጥ ትዕግሥት ትልቅ ቦታ አለው። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ደጋፊ የክለቡን ውጤታማነት እንደሚፈልግ ቢታመንም በመሰል ወቅቶች ግን ደጋፊው ከውጤት ባለፈ መመዘኛ ከቡድኑ ጎን መቆም ይጠበቅበታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 90ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 50ኛ ዓመታቸውን በሚያከብሩበት በዘንድሮው ታሪካዊ የውድድር ዘመን ላይ እንደመገኘታቸው ሁለቱ ቡድኖች በወጣቶች የተሞላ ስብስባቸውን ተጠቅመው ካለባቸው ተጠባቂነት አንፃር በምን ያህል መጠን የታረቀ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል።

