በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ወላይታ ድቻ ከ መቐለ 70 እንደርታ
እስካሁን ባከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች በአራቱም ሽንፈትን በማስተናገድ ደካማ አጀማመርን ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና ሽንፈት አስተናግደው ዋና አሰልጣኙ ገብረክርስቶስ ቢራራን ከኃላፊነታቸውን ካነሱ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። በዛሬው ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት የጦና ንቦቹ በምክትል አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ቀነኒ እየተመሩ ወደ የሚገቡም ይሆናል።
በዋና አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት እየተመሩ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሶስቱ ሽንፈት አስተናግደው በአንዱ ነጥብ መጋራት የቻሉት መቐለ 70 እንደርታዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ እስካሁን ድልን ማሳካት አልቻሉም። ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገምና የዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት በሚያደርገው የዛሬው ጨዋታም በተመሳሳይ በደካማ የውጤት ጉዞ ካሉት ወላይታ ድቻዎች መገናኘቱ ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ፍሬዘር ካሳ በቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ሲሆን በመጠነኛ ጉዳት ምክንያት በመጨረሻው ጨዋታ ያልተሳተፉት ግብ ጠባቂው ሐድሽ በርኸ እና አጥቂው ብርሀኑ አዳሙ ግን አገግመው ወደ መደበኛ ልምምድ ተመልሰዋል።
ቡድኖቹ በሊጉ ለስድስት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም በእኩሌታ ሦስት ሦስት ጨዋታዎቹን ድል አድርገዋል፤ መቐለ 4 ሲያስቆጥር ድቻ 3 ግቦችን አስቆጥሯል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ነገሌ አርሲ
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሊጉ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ በሶስቱ ድል በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው ሽንፈት ሳይቀምሱ ዘልቀዋል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በጎል ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሩ የሆነ አጀማመር ያደረጉት ኤሌክትሪኮች ሶስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆነቸውን ለማስመስከር ነገሌ አርሲን ይገጥማሉ።

በዘንድሮው የውድድር አመት የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን በመሆን የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የተቀላቀሉት ነገሌ አርሲዎች በዋና አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ እየተመሩ በሊጉ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፈው በሁለቱ አቻ መውጣት የቻሉ ሲሆን ሁለት ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ ሰንጠረዥ 15 ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዲስ አዳጊዎቹ በፕሪምየር ሊግ ታሪካቸው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማሳካትም ከጠንካራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ከመሐል ተከላካዩ አብዱላሂ አላዮ እና ከመስመር አጥቂው ቤዛ መድህን ውጭ ሁሉም ተጫዋቾች ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ በነገሌ አርሲ በኩል በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው አማካዩ በረከት ወልዴ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች ዛሬ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ዛሬ ያደርጋሉ።


