ሪፖርት | አራት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ እና ምዓም አናብስት ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | አራት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ እና ምዓም አናብስት ነጥብ ተጋርተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ5 ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ወላይታ ድቻ እና መቐለ 70 እንደርታ ነጥብ ተጋርተዋል።

የምድብ አንድ የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ በነበረው መርሐ-ግብር በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ እንቅስቃሴን ያደረጉበት ነበር። በሙከራ ደረጃም የወላይታ ድቻው ዮናታን ኤልያስ 17ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የቀኝ ክፍል ወደ ሳጥን ይዟት የገባውን ኳስ መቶ የግቡን ቋሚ የመለሳት ኳስ የጦና ንቦቹን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ወላይታ ድቻዎች እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ ቢሆንም ግብ በማስቆጠር የቻሉት ግን መቐለ 70 እንደርታዎች ነበሩ። 28ኛው ደቂቃ ቦና ዓሊ በወላይታ ድቻ ሳጥን ውስጥ የተሰራበት ጥፋት ተከትሎ ያገኛትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቦና ዓሊ ወደ ግብነት ቀይሮም ምዓም አናብስትን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም መለክያዎች የተሻለ እንቅስቃሴና ፉክክር የተደረገበት ሲሆን አጋማሹ ተጀምሮ 9′ ደቂቃዎች ከተቆጠሩ በኋላም መቐለ 70 እንደርታዎች መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ አስቆጥረዋል። በ54’ደቂቃ ኪቲካ ጅማ በመልሶ ማጥቃት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ቡድኑ መሪነቱ ወደ ሁለት ከፍ እንድያደርግ አስችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻዎች የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 70ኛው ደቂቃ ላይም ምንተስኖት ተስፋዬ ከእዮብ ተስፋዬ የተቀበላትን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ ተስፋ የሰጠች እና ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ያስቻለች ግብ ማስቆጠር ችሏል። መደበኛው ሰዓት ተጠናቆ ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃዎች ከማምራቱ በፊትም በመቐለ 70 እንደርታ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል።