በስድስተኛው ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ቀን በምድብ ሁለት ሸገር ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ሸገር ከተማ
የስድስተኛ ሳምንት መርሐግብር በምድብ ሁለት ከቀኑ 9:00 ሲል አርባምንጭ ከተማን ከ አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ ጋር አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራዎችን ሳያስመለክተን የቆየው ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማጥቃቱ ላይ ደካማ የሆኑበትን 45 ደቂቃዎች አሳልፈዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰዓት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የሸገር ከተማው አንተነህ ተፈራ ከ ያሬድ መኮንን ተቀብሎ ወደ ግብ የመታው እና ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ያዳነበት ኳስ የአጋማሹ ብቸኛ ሙከራ ሁኖ ያለ ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጥንቃቄን ምርጫቸው አድርገው የራሳቸውን የግብ ክልል ማስከበሩ ላይ ትኩረት ያደረጉት ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግቶ የጥቃት ኢላማቸውን መሰንዘር ተስኗቸው ረዘም ያለ ደቂቃን ያለ ሙከራ ያስመለከቱን ሲሆን በአርባ ምንጭ በኩል በፍቅር ግዛቸው የግንባር ሙከራ እንዲሁም ሸገር ከተማዎች በቾል ላም እና ያሬድ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ የአርባ ምንጭ ከተማ ተጫዋች ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብነት በመቀየር የማታ ማታ ሸገር ከተማዎች አሸናፊ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ጨዋታውም ሸገር ከተማዎችን 1-0 በሆነ ውጤት ባለድል አድርገዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ምሽት ላይ በተደረገው እና ባህር ዳር ከተማዎች በአጫጭር ቅብብሎች እንዲሁም ኤሌክትሪኮች ደግሞ በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ በተስተዋሉበት ጨዋታ 23ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በስተመጨረሻም አማኑኤል ገብረሚካኤል ለሄኖክ ይበልጣል አሻግሮት አማካዩ ያደረገውን ሙከራ የግቡ ብረት መልሶበታል።
38ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳሮች ሁለት ሙከራዎችን አከታትለው ያደረጉ ሲሆን ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው አሸብር ተስፋዬ ለማራቅ ሲሞክር ያንኑ ኳስ ሄኖክ ይበልጣል አግኝቶት ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ሲቆጣጠርበት ወንድወሰን በለጠ ከረጅም ርቀት ገፍቶ በማመቻቸት እና አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ ዒላማውን አይጠብቅ እንጂ ጥሩ ሙከራ ነበር። በተጨማሪም ክዋቤና ቧቲንግ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አሸብር በድንቅ ሁኔታ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስም በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሲደርሱ የነበሩት የጣና ሞገዶች 54ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ወንድወሰን በለጠ ከግራ መስመር ላይ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ መሬት ለመሬት መትቶ መረቡ ላይ ሲያሳርፈው 81ኛው ደቂቃ ላይም መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ ከገጨው በኋላ አማኑኤል ገብረሚካኤል በማስቆጠር የጣና ሞገዶቹን መሪነት ወደ 2ለ0 ከፍ አድርጓል። ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል


