50 ዓመት የሞላው የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ህልማችን እውን ይሆን ?

50 ዓመት የሞላው የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት ህልማችን እውን ይሆን ?

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከካፍ ፕሬዝደንት ጋር በተለያዮ ጉዳዮች ውይይት እንዳደረጉ ገለፁ።


የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ሀገራችን የማዘጋጀት ጥያቄዋን በተለያየ መልኩ እያቀረበች እንደሆነ ይታወቃል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የዚህ አካል እንደሆነ የሚጠበቅ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያነሳ ውይይት ከካፍ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሲፒ ጋር እንዳደረጉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል።

ከሰዓታት በፊት ባጋሩት ፅሑፍም “ከካፍ ፕሬዝደንት ከዶክተር ፓትሪስ ሞትሲፒ በአፍሪካ እግር ኳስ እና ኢትዮጵያ በእድገቱ ስለሚኖራት ሚና ፍሬያማ ውይይት አድርገናል። ለወጣቶች እድገት፣ የስፖርት መሠረተ ልማት ብሎም የአፍሪካን እግር ኳስ በአለም መድረክ ለማላቅ ከካፍ ጋር ስለሚኖረን ትብብር ተወያይተናል” ብለዋል።


የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ በግሪጎርያን አቆጣጠር በ2029 የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ያቀረቡትን ይፋዊ ጥያቄ ተከትሎ መንግሥት በየአካባቢው ከአነስተኛ እስከ ግዙፍ ስታዲየሞች እየገነባ እንደሚገኝ ይታወቃል። የአፍሪካ እግርኳስ መስራች የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ዋንጫን 1954፣1960 እና 1968 አዘጋጅታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ታላቁ አህጉራዊ ውድድር ካዘጋጀንም ዘንድሮ 50 ዓመት ሞልቶናል።