ሀገራችን ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ 17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ትልቅ ሚና የነበራቸው ተጫዋቾች ለፕሪሚየር ሊጉ ቡድን ፈርመዋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከሦስት ወራት በኋላ በሞሮኮ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወሳል።
በዚህ ቡድን ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ግብ ጠባቂው ተመስገን ከበደ ፣ ተከላካዩ ዘላለም መንግሥቱ ፣ አማካዩ ቢኒያም አብርሃ እና አጥቂው ዳዊት ካሳው ለአዲስ አዳጊው የፕሪሚየር ሊግ ቡድን ሸገር ከተማ ለመጫወት ፊርማቸውን አኑረዋል።
ይፋዊ የፊርማ ስምምነት ርክክብ የፊታችን ቅዳሜ በአንድ ሆቴል (ቦታው ወደፊት በሚጠቀስ) የሚዘጋጅ ሲሆን ቡድኑ የፌዴሬሽኑን የ2029 ግብ የማሳካት እና ወጣቶችን የማብቃት ትልቅ ዕቅድ ይዞ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንደተነሳሳ ከቡድኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ይህንን ዝውውር የRoad to 2029 ፕሮጀክት አባል የነበሩት ዶክተር ኢያሱ መርሐፅድቅ እና የሸገር ከተማ የአካል ብቃት አሰልጣኝና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ዘሩ ሞላ ቀደም ብለው በዕቅድ እንዳመቻቹት ታውቋል።
* ተጫዋቾቹ የውጪ ዕድል የሚያገኙ ከሆነ ቡድኑ ተጫዋቾችን ለመልቀቅ ቅድመ ስምምነት አድርጓል።
* የወላይቻ ድቻ የታዳጊ ቡድን ፍሬዎች የሆኑት ኤፌሶን ኪዳኔ እና አቤኔዘር ዓለማየሁ ወደ ወላይታ ድቻ ዋናው ቡድን ማደጋቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።


