ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት በተደረገው የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ መድን እና ኤሌክትሪክ 1ለ1 ተለያይተዋል።

10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል እየተመራ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የተመጣጠነ ፉክክር የተስተዋለበት ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ መድኖች 12ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው መምራት ችለዋል። ዳዊት አውላቸው ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ኳስ ሲያሻግር ያሬድ የማነ ኳሱን በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ረመዳን የሱፍ በተረጋጋ ሁኔታ አስቆጥሮታል።

 

ከጎሉ መቆጠር በኋላም ቡድኖቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ቢፈልጉም 31ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ አማካይ ዳዊት አውላቸው ከረጅም ርቀት ተሻግሮለት ሳጥን ውስጥ በመድረስ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ሞክሮት ግብ ጠባቂው የሱፍ ሞሮ በቀላሉ ከተቆጣጠረበት ኳስ ውጪ ሌሎች የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር።

ከዕረፍት መልስ 51ኛ ደቂቃ ላይ ከፍጹም ቅጣት ምት ጎሉ ውጪ የጨዋታው የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲደረግ ያሬድ የማነ ከቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በቃሉ አዱኛ  በጥሩ ብቃት አስወጥቶበታል።

በተመሳሳይ የጨዋታ ሂደት ረዘም ላሉ ደቂቃዎች በቀጠለው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች 80ኛ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። አሸናፊ ጥሩነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አብነት ተስፋዬ ግሩም በሆነ መረጋጋት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የማሸነፊያ ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች 82ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው አለን ካይዋ በግንባር በመግጨት ያቀበለውን ኮስ ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በአስደናቂ ሁኔታ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።