በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ተጠባቂ ፍልሚያዎች የተመለከቱ መረጃዎች
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሰባት ነጥቦች በ18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን መነቃቃት በማስቀጠል ከሰንጠረዡ ግርጌ ለመውጣት የሚያደርጉትን ጉዞ ለማሳለጥ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ቢጫ ለባሾቹ በሊጉ ባደረጓቸው 9 ጨዋታዎች 2 ድል፣ 1 አቻ እና 6 ሽንፈቶችን ያስመዘገቡ ሲሆን በሊጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ በኢትዮጵያ ዋንጫ ደግሞ ንብ ላይ ያስመዘገቧቸው ድሎች ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ መነሳሻ እንደሚሆናቸው ይጠበቃል።
በ11 ነጥቦች በ14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ በመቐለ 70 እንደርታ ከገጠማቸው ሽንፈት በፊት የተካሄዱ ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ጥሩ መሻሻሎች ያሳዩባቸው መርሐ-ግብሮች ነበሩ። በተጠቀሱት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን ያሳኩት ቡናማዎቹ በቅርብ ሳምንታት በውጤት ረገድ በሊጉ ያስመዘገቡትን መሻሻል በማስቀጠል ደረጃቸውን ለማሻሻል ብርቱ ፍልምያ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ወልዋሎዎች በዛሬው ጨዋታ ከባድ ጉዳት አስተናግዶ በቅርቡ ቀዶ ጥገና ካደረገው ኢብራሂም መሐመድ ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። የመስመር ተጫዋቾቹ ሰመረ ሀፍታይ እና ፍቃዱ መኮንንም ቅጣታቸው ጨርሰው ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ አማኑኤል አድማሱ ፣ ረጀብ ሚፍታህ እና ይታገሱ ታሪኩ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።
የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 6 ጊዜያት የተገናኙት ቡድኖቹ ኢትዮጵያ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አንድ ጨዋታ ወልዋሎ ድል ሲያደርግ ሁለት ጨዋታዎችን አቻ ተለያይተዋል። ቡና 4 ግብ ሲያስቆጥር ወልዋሎ 2 አስቆጥሯል።
ወላይታ ድቻ ከ ሸገር ከተማ
በዘጠኝ ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ከሰንጠረዡ ግርጌ ለመላቀቅ በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ብርቱ ትግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ባደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ ድል እንዲሁም አራት አራት ጊዜ በእኩሌታ የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች ያስመዘገቡት የጦና ንቦቹ በ9ኛው ሳምንት መርሐ-ግብር በአወንታነቱ የሚጠቀስ መሻሻል አሳይተው በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከምድረ ገነት ሽረ ጋር ነጥብ መጋራት ቢችሉም የዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን ለማግኘት ግን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

ዘንድሮ ወደ ሊጉ አድጎ ጥሩ አጀማመር በማድረግ ላይ የሚገኘው ሸገር ከተማ ደረጃውን ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለመድረግ ድልን እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል። በ12 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገሮች፣ በውድድር ዓመቱ 3 ድል፣ 3 አቻ እና 3 ሽንፈቶችን ማስመዝገብ ችለዋል። ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በ9ኛው ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ሸገሮች ድሉ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥርላቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በጨዋታው ያሳዩትን ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ዛሬም በመድገም ደረጃቸውን ይበልጥ ለማሻሻል ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ፋሲል ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ
በሰንጠረዡ አናት ላይ ከተቀመጠው ሲዳማ ቡና በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብለው በ17 ነጥቦች መሪውን እየተከተሉ የሚገኙት ፋሲል ከተማዎች ድል አድርገው መሪው ላይ ጫና ለማሳደር ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፋሲል ከነማ በሊጉ ሽንፈት ያልቀመሰ ብቸኛ ክለብ ነው፤ በተለይም ሦስት ግቦችን ያስተናገደውና ጥቂት ግቦች በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የመከላከል አደረጃጀት የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። ቡድኑ በ9ኛው ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ አቻ ተለያይቶ ነጥብ ከተጋራ በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስም ብርቱ ፍልምያ ማድረግ ይኖርበታል።
ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ አድጎ ለሊጉ ክስትተ የሆነው ነጌሌ አርሲ በ13 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ በተለይ በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ስታዲየም ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስመዘገበው ሽንፈት አልባ ውጤት ለትልልቆቹ ክለቦች ሳይቀር ስጋት መሆኑን አረጋግጧል። ባለፈው ሳምንትም ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ1 ያሸነፉት ሰጎኖቹ ዛሬም የሊጉን ብቸኛ ሽንፈት አልባ ክለብ ፋሲልን የመርታት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። የነጌሌ አርሲ ወቅታዊ መነቃቃት እና የፋሲል ከተማ ጥንካሬ የዛሬውን ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ፋሲል ከነማ አምሳሉ ጥላሁን፣ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ብሩክ አማኑኤልን በጉዳት፤ ሀብታሙ ተከስተ እና ኪሩቤል ዳኜን በህመም እንዲሁም ቃልኪዳን ዘላለም በቅጣት ከዛሬ ጨዋታ ውጭ ናቸው።በነገሌ አርሲ በኩል አማካዩ ዓብዱልባሲጥ ከማል አሁንም ከጉዳት ባለማገገሙ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በተመሳሳይ ጉዳት ላይ የሰነበተው በረከት ወልዴ ግን አገግሞ ልምምድ የጀመረ ቢሆንም በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ከዚህ በተጨማሪም መጠነኛ ጉዳት የገጠመው አጥቂው ገብረመስቀል ዱባለ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ይህ ጨዋታ በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረግ የመጀመሪያው የሊግ ግንኙነት ነው። ይህ አዲስ ግንኙነት ለሁለቱም ቡድኖች አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እና የበላይነትን ለመያዝ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ይሆናል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
በ14 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀይቆቹ ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ወልዋሎን አንድ ለባዶ ማሸነፍ ከቻሉ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀይቆቹ በመጨረሻውና ጠንካራ ፍልምያ በተደረገበት የመቻል ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ቢችሉም ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ውስን መቀዛቀዞች የሚስተዋሉበት የቡድኑ የፊት መስመር ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ድል ሳያደርጉ ከቆዩ በኋላ በአህጉራዊ ጨዋታ ምክንያት ተራዝሞ በነበረው ተስተካካይ መርሐ-ግብር ሸገር ከተማን 1 ለ 0 ማሸነፍ የቻሉት መድኖች መጠነኛ እፎይታ አግኝተዋል። እስካሁን 3 ድል፣ 3 አቻ እና 3 ሽንፈት ያስመዘገበው መድን ዛሬ ሀዋሳን ማሸነፍ ከቻለ በደረጃ ሰንጠረዡ የሀዋሳን ደረጃ መረከብ የሚችልበት ዕድል ስላለው ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝነት አለው።
ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 31 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 13 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው መድን 6 ጊዜ አሸንፏል። 12 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ሀዋሳ ከተማ 39 ፣ መድን 32 ግቦችን አስቆጥረዋል።

