ምዓም አናብስት ከዋና አሰልጣኙ ጋር ለመለያየት ከጫፍ ደርሰዋል

ምዓም አናብስት ከዋና አሰልጣኙ ጋር ለመለያየት ከጫፍ ደርሰዋል

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያላቸው እህል ውሃ ሊያበቃ ተቃርቧል።

በክረምቱ ከዓመታት በኋላ በሁለት አጋጣሚዎች ወደ አሰለጠኑት የቀድሞ ክለባቸው መቐለ 70 እንደርታ ተመልሰው ላለፉት ወራት ክለቡን በማሰልጠን የቆዩት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት ከጫፍ እንደደረሱ ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ታማኝ ምንጮቿ አረጋግጣለች።

በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታቸው በሊጉ ድል ማስመዝገብ ያልቻሉት አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸው የነበረ ሲሆን በስተመጨረሻውም ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር ለመለያየት ከጫፍ ደርሰዋል።

ሂደቱ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ክለቡ ተተኪ ዋና አሰልጣኝ እስከሚሾም ድረስ በምክትል አሰልጣኞቹ እንደሚመራም ተሰምቷል።