የዐፄዎቹ የመሃል ተከላካይ ቅጣት ተላልፎበታል።
በያዝነው የውድድር ዓመት ፋሲል ከነማ እጅግ ጠንካራ በሆነ የመከላከል አደረጃጀት ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ከአዳማ ከተማ እኩል 3 ጎሎችን ብቻ አስተናግዶ በ20 ነጥቦች ከሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወቃል።
የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው የመሃል ተከላካዩ ምኞት ደበበ ደግሞ ያሳለፍነው ቅዳሜ 10 ሰዓት ላይ ከነጌሌ አርሲ ጋር በተደረገ ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣበት መንገድ እጅግ አነጋጋሪ ነበር።
የጨዋታው 80ኛ ደቂቃ ላይ የነጌሌው ግብ ጠባቂ ኢድሪሱ አብዱላሂ በረጅም ያሻገረውን ኳስ ሀቢብ ከማል ሳይደርስበት ቀርቶ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዎቲ ኳሱን ቢቆጣጠረውም ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ ሀቢብ ኳሱን እንዳያገኘው ጥፋት ሠርተሃል በሚል በዛ ቅጽበት ለኳሱ ሽፋን የሰጠውን ምኞት ደበበን በቀይ ካርድ ከሜዳ ያስወጡት ሲሆን የቡድኑን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳኅሌ ጨምሮ በርካቶች ቅጣቱ እንደሚነሳ ያላቸውን ሙሉ እምነት ሲገልጹ ቢሰነብቱም ዛሬ የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ የውድድር እና ስነስርዓት ኮሚቴ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ምኞት ደበበን “የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች በመማታት” በሚል የአራት ጨዋታ ዕገዳ እና የ3000 ብር ቅጣት አስተላልፎበታል።

በመሆኑም ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ ፣ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የወሳኙን ተከላካይ ግልጋሎት የማያገኝ ይሆናል።


