መረጃዎች | የ12ኛው ሳምንት የመጀመርያ ቀን  ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ12ኛው ሳምንት የመጀመርያ ቀን  ጨዋታዎች

12ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ባለው ፉክክር ውስጥ ወሳኝ የሆነው እና በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያፋልመው መርሐግብር ተጠባቂ ነው።

በ21 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች በነገው ዕለት ሸገር ከተማን ከሚገጥመው መሪው ሲዳማ ቡና በነጥብ ልቀው ለመቀመጥ ዛሬ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ኤሌክትሪክ ይፋለማሉ። በመጨረሻው መርሐ-ግብር ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ዐፄዎቹ እስከ 11ኛው ሳምንት ድረስ ሽንፈት ሳይቀምሱ መዝለቃቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ጥንካሬ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት ካስመዘገቧቸው ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይላቸዋል። ከመጨረሻዎቹ 7 ጨዋታዎች 5 የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ በቀጣይም በፊት መስመር ላይ ያለው የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በ20 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት ሽንፈት ካልቀመሰው ፋሲል ከነማ ጋር ይጫወታሉ። ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በመጨረሻ ደቂቃ በተገኘች ወሳኝ ግብ ሽረ ምድረገነትን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ኤሌክትሪኮች በጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘት ቢችሉም የነበራቸው እንቅስቃሴ ግን በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ነው። በዛሬው ጨዋታም በመጨረሻው መርሐ-ግብር ተጋላጭ የነበረው የኋላ ክፍላቸው ማሻሻል እንዲሁም ለተጋጣሚያቸው ጠንካራ የመከላከል ውቅር በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በፋሲል ከነማ በኩል ቃልኪዳን ዘላለም እና ምኞት ደበበ በቅጣት እንዲሁም አምሳሉ ጥላሁን ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ብሩክ አማኑኤል በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ከአብዱላሂ አላዩ እና አብነት ተስፋየ ውጪ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 9 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 5 ጊዜ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በጎል ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 12 ፋሲል ከነማ ደግሞ 12 ግቦች አስቆጥረዋል።

ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ

በ10 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከስጋት ከቀጠናው ለመራቅ በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ዛሬ ያደርጋሉ።

በሊጉ ለስድስት የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ በመጨረሻው መርሐ-ግብር በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ያስተናገዱት የጦና ንቦቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በተጠቀሰው ዕለት የታዩባቸው ድክመቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል። ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው እንዲሁም ሸገር ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴም መድገም ያልቻለው የፊት መስመራቸውም በብዙ ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በ5 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባል። አሰልጣኝ አሰናብተው ባካሄዱት የመጀመርያ መርሐ-ግብር በቅርብ ተፎካካሪያቸው መቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት ያስተናገዱት አዞዎቹ ከመጥፎው አጀማመር ለመላቀቅ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በሊጉ ድል ማድረግ ያልቻለ ብቸኛ ቡድን የሆነው አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ ከነበረው አቀራረቡ ውስን ለውጦች ማድረግ ቢችልም በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ላይ ያሳየው ብቃት ግን እምብዛም ነው። ይህንን ተከትሎ የተጠቀሱትን ድክመቶች የሚቀርፍ አቀራረብ ማበጀት ከአሰልጣኝ አበባው ቡታቆ ይጠበቃል።

በወላይታ ድቻ በኩል ካርሎስ ዳምጠው እና ኬኔዲ ከበደ አይኖሩም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ እና በርናርድ ኦቼንግ ከጉዳታቸው ለማገገም ረጅም ጊዜ እንደሚወስድባቸው ታውቋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 16 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 9 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች 5 እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ 2 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ባህርዳር ከተማ

በ8 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከስጋት ቀጠናው የሚያስወጣቸውን ድል ለማግኘት ባህርዳር ከተማን ይገጥማሉ።

በተከታታይ ከገጠሟቸው ሽንፈቶች አገግመው ከ8ኛ እስከ 9ኛ ሳምንት ድረስ በተካሄዱ 3 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 9 ነጥቦች 7 በማሳካት መጠነኛ መሻሻል አሳይተው የነበሩት ወልዋሎዎች በመጨረሻው መርሐ-ግብር በነገሌ አርሲ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ከሽንፈት በራቁባቸው ጨዋታዎች በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት የነበራቸው ወልዋሎች ሽንፈት ባስተናገዱበት መርሐ-ግብር ላይ በቂ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወትን ማሻሻልም ደግሞ የዛሬ የቤት ስራቸው ይሆናል።

በ14 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዛሬ ከቢጫዎቹ ጋር ይፋለማሉ። ኢትዮጵያ መድንን ካሸነፉበት የ8ኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት መርሐ-ግብሮች ድል ማድረግ ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹ  ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ድል ለማግኘት በተለይም የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል። ቡድኑ 3 ግቦችን ካስተናገደበት የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ በተከታታይ መረቡን አስከብሮ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ 3 ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመሩ ግን ዘርፈ ብዙ መሻሻሎችን ይሻል።

ነፃነት ገብረመድህን ከቅጣት መልስ ያገኙት ወልዋሎዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ባህርዳር ከተማዎችም በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው ክንዱ ባየልኝ ውጭ ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ለዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ሲገናኙ ባህርዳር ከተማ 2 ወልዋሎ ደግሞ 1 ጨዋታ አሸንፈው በተቀረው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። ባህርዳር ከተማ 4 ወልዋሎ ደግሞ 1 ግብ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ዓ.ም ጨዋታ አልተካተተም)

መቐለ 70 እንደርታ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ7 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከደካማው አጀማመር የሚያላቅቃቸውን ተከታታይ ድል ለማግኘት ከፈረሰኞቹ ጋር ይፋለማሉ።

ከአስር ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ አርባምንጭ ከተማን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁት ምዓም አናብስት በመጨረሻው መርሐ-ግብር የነበራቸውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል እንደሚያልሙ እሙን ነው። በዛሬው ዕለትም በሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ መረቡን አስከብሮ የወጣውን የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ ማዳበር እንዲሁም በተጠቀሰው ጨዋታ አባካኝ የነበረውን የፊት መስመራቸው የአፈፃፀም ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

17 ነጥቦች ሰብስበው 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪዎቹን ለመጠጋት የሚያስችላቸው ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ አቻ እና ሽንፈት በእኩሌታ አንድ ጊዜ ደግሞ ድል ያስመዘገቡት ፈረሰኞቹ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ማሳየት ቢችሉም መሪነታቸው ማስጠበቅ ተስኗቸው ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። በዛሬው ጨዋታም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለው የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነት በመቅረፍ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመራቸው ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

መቐለ 70 እንደርታዎች ጊት ጋትኮችን በቅጣት፤ ሱሌይማን ሐሚድ፣ ብርሃኑ አዳሙ፣ ዘርኢሰናይ ብርሃነ እና አማኑኤል ልዑልን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቤል ያለው ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ሲገለጽ ቢኒያም ፍቅሩ በቅጣት መሳፍንት ጳውሎስ ደግሞ በጉዳይ አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 6 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ጊዜ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 1 ጊዜ ድል አድርገዋል፤  በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹም ፈረሰኞቹ 4፤ ምዓም አናብስት ደግሞ 3 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። (በ2012 የተሰረዘውን ጨዋታ አያካትትም)