ሪፖርት | ዐፄዎቹ በጊዜያዊነት የሊጉን መሪነት ሲረከቡ ቢጫዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ዐፄዎቹ በጊዜያዊነት የሊጉን መሪነት ሲረከቡ ቢጫዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በ12ኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ በአንዋር ሙራድ ብቸኛ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሲያሸንፍ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ባህርዳር ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ዐፄዎች በፈጣን ሽግግር በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ የተጋጣሚዎችን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ ያስተዋልን ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተቃራኒው የሆነበትን የአጋማሹ አካፋይ ሰዓት ድረስ ያለውን የጨዋታ ክፍለጊዜ አሳልፈዋል። ኢላማውን የተጠበቀ ሙከራ በማድረግ ብልጫ የነበራቸው ዐፄዎቹ ዳግም አወቀ እና በረከት ግዛው ከሳጥን ውጪ ሆነው ካደረጓቸው ሙከራውች በተጨማሪ 26ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ብርሃኑ ያለቀ ኳስ አግኝቶ ያመከነበት አስቆጪው አጋጣሚ ይታወሳል። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች በመስመሮች በኩል እየገቡ ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ በሚታይባቸው ደካማ አጨራረስ ምክንያት ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸው አጋማሹ ያለግብ ሊጠናቀቅ ተገዷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጠኑ ተሽሎ በቀረበበት በሁለተኛው አጋማሽ ዐፄዎቹ በቆመ ኳስ ጎል አስቆጥረዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ዋሳዋ ጄኦፊሪ የቆመ ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ኳሱ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ በረከት ወልደዮሐንስ ላይ ተጨርፎ ብቻውን ከነበረው አንዋር ሙራድ ጋር ደርሶ አንዋር ፍፁም በተረጋጋ መንፈስ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ አፄዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጫና ፈጥረው ወደ ሳጥን እየደረሱ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጣጣሩ የተስተዋሉ ሲሆን በተለይም ሀሰን ሁሴን ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ሳይጠቀም የቀረው አጋጣሚ እና እንዲሁም አቤል ሀብታሙ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው ጠንካራው ሙከራ ይጠቀስ እንጂ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአፄዎቹ ተከላካይ እየተቋረጠባቸው ሲቸገሩ እያስተዋልን ጨዋታው አፄዎቹ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን አስቀጥለው በጊዜያዊነት የሊጉ መሪነትም ከሲዳማ ቡና እንዲረከቡ በማድረግ ተቋጭቷል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ባህር ዳር ከተማ

አስር ሰዓት ሲል ጅማሮውን ያደረገው የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ ቢጫ ለባሾቹ ፍፁም ያለቀ ኳስ አግኝተው በማምከናቸው ቶሎ ጎል የሚያስተናግድ እየመሰለ ጅማሮውን አድርጓል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ በቀኝ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ሰመረ ሀፍታይ አሻግሮለት ሰመረ ያለቀ ኳስ ወደ ግብ ቢመታም ኳሱ ኢላማውን እንኳን ሳይጠብቅ የቀረበት አጋጣሚ የቢጫ ለባሾቹ አስቆጪው ሙከራ ነበር። እንደተጠበቀው በሙከራዎች መታጀብ ያልቻለው ጨዋታው 34 ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህርዳር ከተማዎች በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲው ተከላካይ ሱልጣን በርሄ አማኑኤል ላይ በሰራው ከባድ ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣበት ክስተት ይጠቀሳል። አጋማሹም እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለክተን ያለግብ ተገባዷል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲመለስ ባህርዳር ከተማዎች በተጋጣሚያቸው ያለውን የተጫዋች ጉድለት ተጠቅመው ግቦችን ያስቆጥራሉ ተብሎ ሲጠበቁ አጋማሹ እንደታሰበው ሳይሆንላቸው ቢጫ ለባሾቹ በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት እድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውለዋል፤ በተለይም 59ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለባቸው ክስተት ሲታወስ የጣና ሞገዶች ዘለግ ያለ ደቂቃ የግብ ማግባተሸ ሙከራ ሳያደርጉ ሰንብተው 74ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ኳስ አግኝተው በተደጋጋሚ ያደረጉትን ሙከራ የወልዋሎ ተከላካዮች ተረባርበው ካገዱባቸው በኋላ መጠናቀቂያ ላይ የፈጠሩትን እድል ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ሲቸገሩ እያስተዋልን ጭማሪ ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ ወደሳጥን ያሻማው ኳስ ተጨራርፎ ቧቲንግ አግኝቶ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የቢጫ ለባሾቹ ተከላካይ ብሩክ እንዳለ ከመስመር መልሶባቸው ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።