ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ19ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ19ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

19ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ኢትዮጵያ መድን ከ ፋሲል ከነማ

 

የቻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያ መድኖች የአምናውን ቁመናቸውን ማስቀጠል ተስኗቸው በዘንድሮው የውድድር ዓመት ካደረጓቸው የሊጉ ጨዋታዎች በአራቱ ብቻ አሸንፈው እኩል ሰባት ሰባት ጊዜ አቻ እና ሽንፈትን በማስተናገድ በሶስት የግብ እዳዎች አስራ ዘጠኝ ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ጊዜ ድል ካደረገ ሀያ አምስት ቀናትን ያስቆጠረው ቡድኑ ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። የመድኖች ዋነኛ ድክመት ግብ የማስቆጠር ችግራቸው ሲሆን ቡድኑ በ18 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። በአማካይ በየጨዋታው ከ1 ግብ በታች (0.6 ግብ) የሚያስቆጥረው የፊት መስመሩ የዛሬ ተጋጣሚው በሊጉ ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረበት ቡድን እንደመሆኑ ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል።

 

የዛሬውን ጨምሮ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎችን በእጃቸው ይዘው የመጀመሪያውን ዙር መሪ ሆነው የሚያጠናቅቁበትን ዕድል ለማመቻቸት ወደ ሜዳ የሚገቡት ፋሲል ከነማዎች ዛሬ ትልቅ የደረጃ መሻሻል ከሚያስገኙላቸው ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱን ያደርጋሉ። በውድድር ዓመቱ ሽምአንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት በማስናገድ የሊጉ ብቸኛ የሆነው ክለቡ በ7 የግብ ክፍያ 32 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የዐፄዎቹ ዋነኛ ጥንካሬ በ17 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ብቻ ያስተናገደውና በሊጉ ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረበት የመከላከል ክፍሉ ሲሆን ቡድኑ ላይ የሚታየው ግቦችን የማስቆጠር ችግር አስተካክለው ወደ ጨዋታው መቅረብም ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል የቡድን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በፋሲል ከነማ አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት እንዲሁም አቤነዘር ዮሐንስ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ቡድኖቹ በሊጉ 7 ጊዜ ሲገናኙ እኩል ሁለት ሁለቶ ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን 3 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። ሁለቱም ቡድኖች እኩል 4 ጎል ማስቆጠር ችለዋል።

 

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ባህር ዳር ከነማ እስካሁን ካደረጋቸው 18 የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ 4 ጊዜ ድል ቀንቶት፣ በሊጉ ከፍተኛውን የአቻ ውጤት (11 ጊዜ) በማስመዝገብ እና 3 ጊዜ ብቻ ሽንፈትን አቶተናግዶ በ23 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ በመውጣት ነጥብ የመጋራት አባዜ ውስጥ ቢገኝም፣ በ18 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ብቻ ያስተናገደው ጠንካራ የመከላከል ጥንካሬያቸው ግን ሊያስቀጥሉት የሚገባ አወንታዊ ጎን ነው። ይሁን እንጂ ቡድኑ በሊጉ ዝቅተኛ ግቦችን ካስቆጠሩ ክለቦች ውስጥ አንዱ ነው፤ በጨዋታ በአማካይ 0.6 ግብ ብቻ የሚያስቆጥረው ደካማ የማጥቃት ክፍሉም 12 ግቦችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን ይህ ድክመትም በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ሊታረም የሚገባው ዋነኛ ድክመቱ ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 4ቱን አሸንፎ፣ 8 ጊዜ አቻ በመውጣት እና 6 ጊዜ ተሸንፎ በ20 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሀምራዊ ለባሾቹ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ በሶስቱ ተሸንፈው መጥፎ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በ18 ጨዋታዎች 22 ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍላቸው ደግሞ የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ነው። ቡድኑ 20 ግቦችን ያስቆጠረና የተሻለ ግብ የማስቆጠር ብቃት ያለው የፊት መስመር ቢኖረውም ያልተረጋጋው የመከላከል አደረጃጀቱ በጨዋታዎች ሽንፈት እንዲያስተናግድ እያደረገው ይገኛል፤ የኋላ ክፍሉ ማሻሻልም የቡድኑ ቀዳሚ የቤት ስራ ነው።

ባህር ዳር ከተማ ዛሬም አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ክንዱ ባየልኝን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄን ደግሞ በቅጣት ምክንያት የሚያጣ ይሆናል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ቢንያም ካሳሁን እና ዮናስ ለገሰ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ክለቦቹ በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታዎች ድል ሲያደርጉ የተቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

 

23 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ያስተናገዱበትን ደካማ ጉዞ ለመቀልበስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የተቸገረ ሲሆን በተለይም ግብ የማስቆጠር ብቃቱ ቀንሶ በሦስት ጨዋታዎች ላይ ኳስ እና መረብን ሳያገናኝ ወጥቷል። ሆኖም ባለፉት አራት የእርስ በርስ ግንኙነቶች ሶስት ጊዜ ተጋጣሚውን ማሸነፍ መቻሉ ለነገው ጨዋታ እንደ ትልቅ ስነ-ልቦናዊ ብልጫ የሚወሰድ ሲሆን ፈረሰኞቹ ወደ ድል ለመመለስና ደረጃቸውን ለማሻሻል በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን የማጥቃት ክፍላቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

በ16 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች
በስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ በመጨረሻው ሳምንት በአርባ ምንጭ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው የውድድር ዓመቱ 8ኛ ሽንፈታቸውን አስመዝግበዋል። በዛሬው ጨዋታም ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ከፈረሰኞቹ ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን በቅርቡ ሀዲያ ሆሳዕናን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ተስፋ ቢያገኝም ዛሬ በነብሮቹ የተቀዳጁትን ድል ለመድገም የአጥቂ ክፍሉን ውጤታማነት ማሻሻል ቀዳሚ ስራቸው ሊሆን ይገባል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አሚኑ ነስሮ በወልዋሎ በኩል ደግሞ ሰመረ ሀፍታይ በቅጣት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 5 ጊዜያት ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ሲያሸንፍ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 4 ሲያስቆጥሩ ቢጫ ለባሾቹ 3 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ እንዲሁም በ2011 ሁለተኛው ዙር ላይ ያልተካሄደው ጨዋታ አልተካተተም)

 

ነገሌ አርሲ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በ18 ጨዋታዎች 32 ነጥቦችን በመሰብሰብ በሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነገሌ አርሲዎች፣ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን በማሸነፍ እጅግ አስደናቂ አቋም ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ በመጨረሻው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 0 በማሸነፍ የመሪነቱን ፉክክር አጥብቆ የቀጠለ ሲሆን ጠንካራ የመከላከል አቅሙና ውጤት የማስጠበቅ ብቃቱ የስኬቱ ቁልፍ ጥንካሬዎች ናቸው። ነገሌ አርሲዎች ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ያላቸውን የ3 ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና የመጀመሪያውን ዙር ከመሪዎቹ ጎራ ሆነው ለማጠናቀቅ ውጤታማው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸውን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

በተቃራኒው 19 ነጥቦችን ይዘው በ17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ድል እና አምስት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ሽንፈት ሳይቀምሱ የዘለቁ ሲሆን ከደካማ አጀማመር መሻሻል እያሳዩ ይገኛሉ።።ቡድኑ ምንም እንኳን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጨምሮ ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ ቢችልም ካለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱ በመከላከሉ ረገድ ያለውን ጥንካሬ ማሳያ ነው። ሆኖም ቡድኑ አሁንም ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የፊት መስመሩን ውጤታማነት ማሳደግ ግድ ይለዋል።

ነገሌ አርሲዎች ጉዳት ላይ ካለው ዓብዱልባሲጥ ከማል በተጨማሪ በቅጣት ምክንያት የከቤ ብዙነህን ግልጋሎት አያገኙም።መቐለ 70 እንደርታዎች ጉዳት ላይ ከሰነበቱት ዘርኢሰናይ ብርሀነ እና ሱሌይማን ሐሚድ በተጨማሪ ፍፁም ዓለሙ እና ብርሀኑ አዳሙን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱም ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ መድረክ የሚገናኙ ይሆናል።