“የእኛ ክለብ በጀት አይደለም ያለው፣ ድጎማ ነው። እኛ እቅድ አውጥተን ሰለሰጠን አይደልም ገንዘብ የሚመደብለን። እንደራሴዎቹ በሰብጀክቲቭ ዌዬ /መረጀ ላይ ባልተንተራሰ አሰራር/ ‘ይህ በጀት ይበቃችኋል’ ብለው የሚፈቅዱት። ከዛም፣ ያ የተፈቀደውም ገንዘብ በወቅቱ አይለቀቅም። 50 ሚሊዮን ቢፈቅድ፣ አሁን አስሩን ሰጥቶህ፣ የሚቀጥለው ምን ያህልና መቼ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆነህ መናገር አትችልም”
በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለቤትነት፣ በፊት ኮርነር ስፖርት ኮንሰልታሲ አስተባባሪነት እና በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የቡድን መሪነት፣ ከ90 በላይ የሚሆኑ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት (ከፌዴሬሽንና ሊጉ አመራሮች ጀምሮ እስከ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎችና ጋዜጠኞች) በማሳተፍ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጥልቅ ጥናት መነሻ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦችን መሰረታዊ ችግሮች በክፍል አንድ ጽሁፍ መቅረቡ ይታወሳል።

ባለፈው ጽሁፍ ከጥናቱ ግኝቶች መካከል ሦስቱ አንኳር ተግዳሮቶች ቀርበዋል፤ እነሱም፦ ክለቦች የአካባቢያዊ መንግስታት (የፋይናንስ) ጥገኛ መሆናቸው ፣ የመንግስት እጅ በጉልህ የሚታይበት የአመራር አደረጃጀት ችግር እና የክለቦቹ ተቋማዊ ቁመና ደካማ መሆን ነበሩ። እነዚህ ሦስት አንኳር ነጥቦች የእግር ኳሳችንን መዋቅራዊ ስብራት እና የችግሩን ያሳዩን ናቸው። ይሁን እንጂ የጥናቱ ግኝቶች በእነዚህ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። በዛሬው የክፍል ሁለት ተከታታይ ፅሁፍ፣ ከጥናቱ የተገኙ ተጨማሪ ተግዳሮቶች ቀርበዋል። በመጀመሪያው ክፍል ሦስት ዋና ዋና ችግሮች የተዳሰሱ ሲሆን፣ የዛሬው ምልከታ የሚጀምረው በጥናቱ ከተለዩት የክለቦቻችን ማነቆዎች መካከል አራተኛው ከሆነው ተግዳሮት ነው።
የበጀት ዕቅድ እና አጠቃቀም ጉድለት
ክለቦች የበጀት ዕቅድ እጦት እና የበጀት አጠቃቀም ጉድለት እንዳለባቸው በተደረጉት ቃለመጠይቆች ጎልቶ የተነሳ ሌላው ነባራዊ እውነታ ነው። ክለቦች በጀታቸውን ከዓመት በላይ መተንባይ ባለመቻላቸው እና ልማታዊ ስራ ላይ ከመሰራት መገደባቸው የአገራችን እግር ኳስ ከሚኖርባቸው ነባራዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ መሆኑን በስፋት ተነግሯል። በርካታ የጥናቱ ተሳታፊዎች ተመክሮዋቸውን እንዳካፈሉት፣ ክለቦች በከንቲባ፣ በዞን አስተዳደር፣ ወይም በክልል አስተዳደር ይሁንታ በሚለቀቅ በጀት የሚተዳደሩ በመሆናቸው፣ ከአንድ አመት ያለፈ እቅድ ይዘው መቅረብ የሚችሉበት ቁመና ኖሯቸው አይስተዋሉም። በመሆኑም፣ የአመት በጀት ይዘው፣ ለቀጣዩ አመት ሊያሻግራቸው የሚችል ገንዘብን ለማሰባሰብ አስቀድመው የሚንቀሳቀሱበት አሰራርን ማደርጀት የእግር ኳሱ አመራር አካል ሃላፊነት እንደሚሆን እና ለዚህም በሞያው የሰለጠነ የሰው ሃይል ማደራጀት የግድ እንደሚል በአጽዕኖት ተጠቁሟል። በእኩሌታውም፣ አስቀድሞ ያልተያዘ እና በአግባቡ ያልተወጠነ የወጪ አይነት ሲተገበር ማየት የተለመደ መሆኑን የተወሰኑ ተሳታፊዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ያጋሯቸው እንኳር ነጥቦች በጥቅሉ የሚከተሉት ናቸው፦ ከተጫዋቾች ክፍያ የዘለለ በጀት አለመቅረጽ፣ የፋይናንስ አቅምን ያላገናዘበ የክፍያ ስምምነት ውስጥ መግባት ፣ ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ክፍያዎች ላይ ውሳኔ የመስጠት ተነሳሽነት መጉደል፣ በጊዜያዊ ትኩሳቶች ተነሳስቶ እቅድ ውስጥ ያልተካተተ ክፍያ መፈጸም፣ እና በወቅቱ ክፍያዎችን አለመፈጸም የሚሉ ናቸው። የበጀት ዕቅድ እጦትን በሚመለከት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የባለ ድርሻ አካላት መካከል የክለብ አስተዳዳሪዎች ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ጉዳዩን አስመልክቶ አንድ አስተዳዳሪ ያካፈሉት አተያየት የሌሎች ተሳታፊዎችን እይታ በሚያንፀባርቅ መልኩ ያስቀምጠዋል፦ “የእኛ ክለብ በጀት አይደለም ያለው፣ ድጎማ ነው። እኛ እቅድ አውጥተን ሰለሰጠን አይደልም ገንዘብ የሚመደብለን። እንደራሴዎቹ በሰብጀክቲቭ ዌዬ /መረጀ ላይ ባልተንተራሰ አሰራር/ ‘ይህ በጀት ይበቃችኋል’ ብለው የሚፈቅዱት። ከዛም፣ ያ የተፈቀደውም ገንዘብ በወቅቱ አይለቀቅም። 50 ሚሊዮን ቢፈቅድ፣ አሁን አስሩን ሰጥቶህ፣ የሚቀጥለው ምን ያህልና መቼ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆነህ መናገር አትችልም” ብለዋል።
በተመሳሰለ መልኩ፣ ሌላ አስተዳደር ፣ የክለቦች የፋይናንስ አቅምን ያላገናዘበ የክፍያ ስምምነት ውስጥ መግባት እና ክፍያዎችን በወቅቱ አለመፈጸምን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ክፍያዎች ላይ ውሳኔ የመስጠት ተነሳሽነት እንደሚጎድል ተመክሯቸው እንዳስተማራቸው ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል። በሃብት አጠቃቀም ዙሪያ ገንዘብ እንዴት፣ ለምን እና መቼ ማውጣት እንዳለባቸው የመወሰን እንከን በተደጋጋሚ እንደሚስተዋልባቸው ተጠቅሷል። ይህን በተመለከተ አንድ በአሰልጣኝነት ሞያ የተሰማሩ ተሳታፊ ያካፈሉት እይታ በርካቶች ያነሱትን ሃሳብ ጠቅለል አድርጎ ያመላክታል፦ “የክለቦች በጀት ከሆድ ያለፈ ሊሆን ይገባል፤ ማለትም ከደሞዝ፣ ሆቴል፣ እና ትራንስፖርት ወጪ አልፎ የልማት ስራ ላይ ሊውል ይገባል። የልምምድ ሜዳ፣ የማደሪያ ካምፕ መገንባት መጀመር አለባቸው። በዚህ በኩል፣ ወደ ክለቦች የሚመጡት ሰዎች የረጅም ጊዜ ራዕይ ያላቸው ናቸው ማለት ያስቸግራል። የረጅም ጊዜ ራዕይ የሚኖረው ክለብ፣ ታዳጊዎች ላይ ይሰራል። እኛ አገር ግን የውጭ ተጫዋቾችን በከፍተኛ ክፍያ መቅጠር ይመረጣል። እነሱ ሲሄዱ ክለቦቹ ባዶ ይሆናሉ።
… በርካታ ስመ ገናና እና ተወርተው የጠፉ ከአስር በላይ ክለቦች ልጠቅስልህ እችላለሁ፦ የአየር መንገድ፣ አየር ሀይል፣ ኪራይ ቤቶች፣ ሙገር፣ ባቡር፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ብርሃነ ሰላም፣ ትራንስ፣ ሃረር ቢራ፣ ጉና፣ ዳሽን ቢራ፣ ወንጂ፣ መተሃራ፣ የተወሰኑት ናቸው። እኝህ ክለቦች የታጠፉበት አንዱ እና ዋነኛው ምክኒያት … የበጀት አጠቃቀም ጉድለት ተጽዕኖ ነው” ብለዋል።
ምክረ-ሃሳብ፦ ክለቦች ቢያንስ የሶስት ዓመት የበጀት እቅድ ነድፈው፣ ለክትትል እንዲያግዝ፣ በሚመለከትው የመንግስት አካል አጸድቀው ለሊጉ ሊያቀርቡ ይገባል። በየአመቱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ለአዲስ ዓመት ውድድር ሲመዘገቡ፣ በሁሉም የቦርዱ አባሎቻቸው የተፈረመበት እና በአመራር አባላቱ የፀደቀ በጀት ለሊጉ ሊቀርብ ይገባል። እንደ አማራጭም፣ አስቀድመው የሚከፍሉትን ገንዘብ ባንክ ውስጥ መኖሩን የክለቡን የባንክ አካውንት የሚገልጽ ደብዳቤ በማቅረብ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት
የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የአገራችን ክለቦችን በሚመለከት በቀዳሚነት ከተነሱት ችግሮች መካከል አንዱ ነው። የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ክለቦች የተጫዋች ደሞዝ፣ የፊርማ ክፍያ፣ የቦነስ ክፍያ፣ የመሳሰሉ አከፋፈሎችን በሚመለከት ግልጽነት እና ተጠያቂነታቸው ሊፈተሽ እንደሚገባ በሰፊው አንስተውታል። እንደ በርካቶቹ እይታ፣ ለተጫዋቾች ዝውውር የሚከፈለው የክፍያ መጠን ከስፖርቱ እድገት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ሆኖ አይታይም፡፡ በተዛመደም፣ አንዳንድ ክለቦች ከአላቸው የፋይናንስ አቅም በላይ ለማውጣት እንደሚነሳሱ እና ቃል እንደሚገቡ፣ ነገር ግን የውድድር ዘመኑ እየገፋ ሲሄድ ቃላቸውን ማከበር እንደሚፈታተናቸው ተሳታፊዎች አንስተዋል።
በጥናቱ የተሳተፈ ጋዜጠኛ አንዳስቀመጠው፡ “ክለቦች እንዲፈርሱ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የፋይናንስ አስተዳደር ጉድለት ነው። በተለይ፣ ያልተመጣጠነ ወጪ፤ [በተለያዩ ዓመታት የተለያዩ] ክለቦች የፋይናንስ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ማየት የተለመደ ነው፣ ይህን ለማስቀረት እንደ የገንዘብ ጨዋነት ደንብ (ፋይናንሺያል ፌር ፕሌይ) የዝውውር ወጭን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ፣ ክለቦች የሚሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ ለእግር ኳሱ እድገት እያዋሉ መሆኑን መቆጣጠር ጠቀሜታው ለ[እግር] ኳሱ ነው፤ ተጨማሪ ትርፍ እንደማግኘት ይሆናል” ብሏል። አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ክለቦች በአመት ያገኙት የገንዘብ መጠን፣ ያወጡት መጠንና ለምን ወጭ እንዳደረጉት በትክክል በገለልተኛ አካል ኦዲት መደረግና የፋይናንስ አፈፃፀም ለሊጉ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ እይታቸውን አካፍለዋል። በዚህ ዙሪያ፣ የፋይናንስ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን በሚመለከት ክለቦች የባንክ አካውንታቸው፣ የገንዘብ አያያዛቸው፣ የሃብት አስተዳደራቸው፣ በተሳታፊዎቹ ዘንድ በተደጋጋሚ የተነሱ ትኩረት የሚሹ ነጥቦች ናቸው።
ከባንክ አካውንት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ እይታዎች የቀረቡ ሲሆን አንድ የክለብ አሰተዳደር ያጋሩት ምልከታ የብዙዎቹን ተሳታፊዋች አተያይ የሚያንፀባርቅ ነው፦ “በርካታ ክለቦች የራሳቸው የባንክ አካውንት የላቸውም። ለምሳሌ፣ የክለብ [ሃለመ] የባንክ አካውንት በከተማው የፋይናንስ መምሪያ ስር ነው። ነገር ግን ክለቡን ሄደህ የራሳችሁ ባንክ አካውንት አላቹህ ወይ ብለህ ብትጠይቅ አዎ ነው የሚሉህ፤ ይህ ሊፈተሽ የሚገባ ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ዋነኛው መሰናክል የፋይናንስ አስተዳደር ችግር ነው።” በተመሳሳይ የገንዘብ አያያዝን በሚመለከት በጥናቱ የተሳተፉ አንድ ዳኛ እንደገለፁት “የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነት ያስፈልገዋል። አበል፣ ደመወዝ፣ የሆቴል ወጭ፣ ኮሚሽኖች፣ ተጠያቂነት በሚያረጋግጥ የገንዘብ አጠቃቀም ደንብ መመራት አለባቸው”።
የሃብት አስተዳደራቸውን አስመልክቶ የተሰጡ በርካታ አተያየቶችን ሌላ ዳኛ የጥናቱ ተሳታፊ ያካፈሉት እይታ የሚያንጸባረቅ ይሆናል፦”የኛ ክለቦች ደሃ ናቸው ማለትም ይከብዳል። ችግራቸው የቪዥን ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፦ እንደ መሬት ያለ ሃብት በእጃቸው ሆኖ ብዙዎቹ የተሰጣቸውን ቦታ አጥረው ከማስቀመጥ ያላለፉ አሉ። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ እና ወደ ገንዘብ መቀየር የሚችሉ የክለብ ደጋፊዎችም የባከኑ ሃብቶች ናቸው። ክለባቱ ሃብታቸውን የሚያስተዳድሩበት አቅም እና እውቀቱ ያንሳቸዋል” ብለዋ። በርከት ያሉ ተሳታፊዎች፣ በጥያቄ መልክም ያነሱት ተያያዥ ርዕሰ ጉዳይ የተጫዋቾች ደሞዝ ሚስጥራዊነት ነው።
ምከረ ሃሳብ፦ የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነትና ተጠያቂነትን በሚመለከት ዝርዝር ምክረ-ሃሳብ በጥናቱ የቀረበ ሲሆን፣ ለጥቆማ ያክል፦ በውጭ ገለልተኛ ኦዲተሮች ማስመርመር ፦ ክለባቱ ወጥ የሆነ የገለልተኛ ኦዲት ስርዓትን እንዲከተሉ በመጠየቅ፣ የተለመደውን በገለልተኛ የውጭ ኦዲተሮች የሚከናወን አመታዊ የሂሳብ ምርመራ ማካሄድ ይመከራል። አማራጭ በጀት ማቅረብ ፦ ክለባት፣ ያለፈውን የውድድር ዓመት የኦዲት ሪፖርት ብቻ ሳይሆን፣ የመጪውን የውድድር ዘመን በጀት ሲያቀርቡ ብቻ ነው ክለቦች የሊግ የገቢ ክፍፍሉ ድርሻቸው ሊለቀቅ የሚገባው።
የኦፊሻል የባንክ አካውንት ሰነድ ማቅረብ፡- እያንዳንዱ የሊጉ አባል ክለብ በአገሪቷ ውስጥ በሚንቀሳቀስ ባንክ የተመዘገበ የራሱ የሆነ የእግር ኳስ ክለቡ የባንክ አካውንት ማቅረብ አለበት። አካውንቱም የክለቡን ስም እና አድራሻ በግልጽ የሚያሳይ፣ እና በክለቡ ሙሉ አስተዳዳር እና ቁጥጥር ስር መሆኑን የሚገልጽ መሆን አለበት። የሚቀርቡ አመታዊ ሰነዶችን ማሳወቅ፡ – ክለቦች በጀታቸውን፣ አማራጭ በጀታቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ አባል ክለባት በገለልተኛ የውጭ ኦዲተር የተከናወነ የኦዲት ሂሳብ ሪፖርታቸውን በየዓመቱ ከ__ቀን እና ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የኦዲት ሪፖርቱን ሲያቀርቡ ብቻ፣ ከሊጉ የሚችለውን የገቢ ክፍፍል ድርሻ ሊያገኙ የሚገባቸው። የፋይናንስ መመሪያውን የሚተላለፍ ክለብ ቅጣትን ማሳወቅ፦ አንድ አባል ክለብ የሊጉን የፋይናንስ መመሪያ በሚተላለፍበት ጊዜ የተለያዩ መቀጫዎች እርምጃዎች ሊወሰድበት ይችላል።
የሰለጠነ የሰው ሃይል (አስተዳደራዊ) እጥረት
በርካታ የአገራችን እግር ኳስ ክለቦች በክህሎትና በእውቀት ላይ የተመሰረቱ እና በመስኩ በሰለጠነ የሰው ሃይል የተደራጁ ባለመሆናቸው፣ በዘልማድ እንደሚመሩ የጥናቱ ተሳታፊዎች እይታቸውን በተደጋጋሚ አጋርተዋል። በእኩሌታውም፣ ለክለባቸው ያለመታከት የሚሰሩ የክለብ አስተዳደር ሰራተኞች መኖራቸውን ነገር ግን እኝሁ ሰራተኞችም በሞያው ያልሰለጠኑ መሆናቸው የራሱን ተጽዕኖ በአገራችን የእግር ኳስ ክለቦች ላይ እንዳሳደረባቸው በስፋት ተነስቷል።
አብዛኛውን ጊዜ ስልጠናዎች በዳኞች እና በአሰልጣኞች ዙሪያ ላይ እንደሚያተኩር እና የክለቦች አስተዳደርን በሚመለከት የሚዘጋጁ ስልጠናዎች የሌሉ መሆናቸውን የጥናቱ ተሳታፊዎቹ አያይዘው ጠቁመዋል። በእነዚህ እና ሌሎች ተዛማጅ ምክኒያቶች፣ የክለባት አደረጃጀት በስፖርት አስተዳደር ሞያ በሰለጠኑ ባለሞያዎች ሊደራጅ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተነስቷል። እንደ ባለ ድርሻ አካላቱ ምልከታ፣ በሞያው የሰለጠኑ አስተዳደሮች በቦታው ላይ መቀመጥ፣ ክለባቱ የጠነከረ መሰረት እንዲይዙ እና ስኬታቸው ዘላቂነት እንዲኖረው ያስችላል። ይህ እይታ፣ በተለይ በኮሚሽነሮች፣ በዳኞች፣ በክለብ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ እና በአሰልጣኞች ዘንድ በስፋት ተነስቷል።
ክለቦች ያሏቸው ውሱን ሰራተኞችም ሌሎች የመንግስት ሃላፊነቶችን ደርበው እንደሚሰሩ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል። በርዕሱ ላይ በርካታ ተመሳሳይ እይታዎች የተጋሩ ሲሆን፣ በማሳያነት አንድ በማሰልጠን ሞያ የተሰማሩ ተሳታፊ ያካፈሉት እይታ ቀርቧል። አሰልጣኙ እንዳስቀመጡት፦
“ክለቦች አንድ ግለሰብ ሁሉን ስራ እንዲሰራ የሚደረግበት የዋን ማን ሾው /one man show/ ናቸው። ሲከፋም፣ አንዳንድ የክለብ ስራ አስኪያጆች ከእግርኳስ በተጨማሪ ሌላ ስራ ደርበው የሚሰሩ እና የሙሉ ጊዜ የእግር ኳስ ክለቡ ሰራተኛ ያልሆኑ አሉ። … የስራ መደበላለቆች አሉ። አብዛኞቹ ክለቦች በአንድ ስራ አስኪያጅ እና በአንድ ጸሃፊ ብቻ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ አንድ ቢሮ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ናቸው። ይሄ ስራ አስኪያጅ ስንት ነገር ሊሰራ እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል። ከተጫዋቾች ጋር ያለን ጉዳይ ሲፈታ ቀኑን ይጨርሳል። ፌስቡክ ላይ ይለጥፋል፣ የቡድን መሪ ይሆናል፣ የቴክኒክ ዳሬከተር ሆኖ ይሰራል፣ ለገቢ ማሰባሰብ እና እቅድ ለመንደፍ ጊዜውም አቅሙም አይኖረውም” ብለዋል። ብዙዎቹ ተሳታፊዎች፣ የስፖርቱ ከፍተኛ አመራር አካል በቀጣይ ሂደት ውስጥ ችግሩን የመቅረፍ ሃላፊነት እንዳለበት አመልክተው፣ በክለቦች የአቅም ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መተግበር እንዳለባቸው አካፍለዋል።
ምክረ ሃሳብ፦ በአገራችን እግር ኳስ ሃላፊነት ያለበት ከፍተኛ አካል ክለቦች ድርጅታዊ መዋቅር ተከትለው የሰው ሃይላቸውን እንዲያሟሉ ሊጠይቅ ይገባል፣ የሚቀረጹ ፕሮግራሞችን ወደ ተግባር ለመቀየር፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርትም ይህን ይጠየቃል። ብሎም ክለቦቹ ለሚያሟሏቸው የስራ መደቦች የሰው ሃይል የሞያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲዘጋጅላቸው ሊያደርጉ ይገባል። በመሆኑም፣ መሰረታዊ የሆኑ የስራ መደቦችን በአጭር ጊዜ ዕቅድ ውስጥ በሰው ሃይል መሟላት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚጋባ ሃላፊነት ነው።
ለዚህም የሞያ ማሻሻያ ስልጠና አስፈላጊነት በተሳታፊዎቹ በስፋት ተነስቷል፤ በተለይ የክለብ አመራር አካላት ስልጠና እንዲያገኙ በርካታ እይታዎች ቀርበዋል። በሃላፊነት ላይ ያሉት የክለብ ስራ አስኪያጆች የሰው ሃይል አስተዳደር እና የገቢ ማመንጫ የሞያ ማሻሻያ ስልጠና ሊሰጣቸው የግድ ይላል። ግብን ማስቀመጥ እና ተነሳሽነት መኖሩ የመጀመሪያ ርምጃ ሲሆን፣ ተነሳሽነቱን ወደ መሬት እንዲወርድ የሚያስችሉ ባለሞያዎችን ማፍራት ለግቡ መሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የኢትዮጵያ ክለቦች ችግሮች ዘርፈ ብዙ ነው። ጽሁፉ በተከታታይ ክፍሎች የተሰናዳ ነው። ከተለምዷዊ አሰራር ተላቀው ዘመናዊ ተቋማት እንዲሆኑ ይህ ጥናት በስፋት ዳሰሳ አድርጓል። በክፍል ሶስት የጥናቱን ቀጣይ ግምገማ እናቀርባለን።
ስለ ፀሀፊው፦
ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ እንዲሁም በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል የ5 ዶክትሬት ተማሪዎች አማካሪ ናቸው። ዶ/ር ጋሻው በስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። እስካሁን 10 መፅሀፍትን አሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢዎች አቅርበዋል።

