የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊ እንደሆነ የሚነገርለት አንበሉ ብሩክ ታረቀኝ በአሳዳጊው ቤት ለመቆየት ተስማምቷል።

አስቀድመው የብሩክ እንዳለ እና የተመስገን ብርሃኑን እና መስመር አጥቂውን ቢላል ገመዳን ዝውውር ማጠናቀቅ የቻሉት እና የመስመር አጥቂውን ፀጋ ከድር ውል ያራዘሙት ፈረሰኞቹ አሁን ደግሞ የብሩክ ታረቀኝን ውል አራዝመዋል።
መነሻውን በፈረሰኞቹ ታዳጊ ቡድን በማድረግ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው እና ዕድገቱን ጠብቆ ክለቡን ያለፉትን ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ፤ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የቡድኑ አምበል በመሆን በሠላሳ ስድስት ጨዋታዎች ላይ 3195 ደቂቃዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በአሳዳጊ ቤቱ ለመቆየት መስማማቱን አውቀናል።
ብሩክ ከተጫዋችነት ባሻገር የክለቡ የልብ ደጋፊ በመሆን የአባልነት መታወቂያ ከልጅነቱ ጀምሮ ያወጣ መሆኑ ይታወቃል።

