ኢትዮጵያ መድን አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

ኢትዮጵያ መድን አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

የ2017 የሊጉ ቻምፕዮን ኢትዮጵያ መድን አዲስ አሰልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች

ኢትዮጵያ መድን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ያስቻሉት አሰልጣኝ ገብረመድን ሀይሌ ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ውላቸው መጠናቁን ተከትሎ ክለቡ ለማቆየት ቢፈልግም አሰልጣኙ ሀሳቡን ባለመቀበል በክብር መለያየታቸውን አስቀድመን ገልፀን ነበር።

የክለቡ ቦርድ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሰሞኑ ስብሰባ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን የስራ ልምዳቸውን ያስገቡ ሦስት አሰልጣኙችን ሲመረምር ቆይቶ በመጨረሻም አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ለመቅጠር መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በእግር ኳስ ተጫዋችነት በስድስት ክለቦች ተጫውቶ ያለፈው እና ወደ አሰልጣኝነቱ ከገባ በኋላ በመተሀራ እና አካባቢዋ በርካታ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀውና የአሰልጣኝነት ህይወትንም የመተሀራ ቡድንን በመያዝ በኋላ በአዳማ ከተማ ረዳት እንዲሁም ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ሲሆን በሀምበሪቾ ቆይታውም ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎ በፕሪምየር ሊጉ በዋና አሰልጣኝነት ማገልገሉ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም በተጠናቀው የውድድር ዓመት በወላይታ ድቻ ምክትል ሆኖ መስራቱ ይታወቃል።