የቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን የተሻገሩ ሀገራት ታውቀዋል

የቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን የተሻገሩ ሀገራት ታውቀዋል

የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቀቀ

በፊፋ ደረጃ መሰረት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ አስራ ሁለት ሀገራት የተሳተፉበት የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቋል። በድምር ውጤት ሳኦቶሜ ፕሪንሲፔን አራት ለባዶ የረታችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲ፣ ሌሴቶ፣ ኤርትራ እና ሶማልያም ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ምድብ ድልድሉ የተቀላቀሉ ሀገራት ሆነዋል። በዚህ መሰረት የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ውድድር የተጠቀሱት 6 ሀገራት እና በቀጥታ በምድብ ድልድሉ የሚካፈሉ 42 ሀገራት ጨምሮ 48 ቡድኖች ይካፈሉበታል።

ከነሐሴ 2018 እስከ መስከረም 2019 ባለው ጊዜ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ውድድር ከሦስት እስከ አራት ሀገራት ባቀፉ 13 ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ምድባቸውን በበላይነት ያጠናቀቁ 13 ቡድኖች እንዲሁም 3 በምርጥ ሁለተኛነት ማጣሪያውን ያገባደዱ ብሔራዊ ቡድኖችም በቀጥታ በአፍሪካ ዋንጫው ይሳተፋሉ። የተቀሩት በየምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ 10 ቡድኖች ደግሞ በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አከናውነው አሸናፊዎቹ 5 ሀገራት ወደ ውድድሩ የሚያመሩ ይሆናል።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2000 ጋና እና ናይጄሪያ እንዲሁም በ2012 ጋቦን እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በጣምራ ካዘጋጇቸው ሁለት ውድድሮች ውጭ በጣምራ ውድድሮችን የማዘጋጀት ታሪክ የሌለው የአፍሪካ ዋንጫ በ2027 በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
በሦስት ሀገራት የሚዘጋጅ ይሆናል፤ ጎረቤት ሀገራት ኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ደግሞ ድግሱን የማዘጋጀት ኃላፊነት የተረከቡ ሀገራት ናቸው።