ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

27ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ይጀምራል። የዕለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች ደግሞ እንደሚከተለው አዘጋጅተናል
.

ሸገር ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

ጊዮርጊስ እና ሀዲያን በማሸነፍ ጥሩ እያገገሙ የነበሩት ሸገር ከተማዎች ከዛ በኋላ ግን በአርባምንጭ ሲሸነፉ ከኢትዮጵያ ቡና አቻ ተለያይተዋል። በተለይ በመጨረሻው ጨዋታ በአሚር አብዶ ግብ አማካኝነት እየመሩ የነበሩት ሸገሮች 66ኛው ደቂቃ ላይ ገዛኸኝ ደሳለኝን በቀይ ካርድ አጥተው በኋላም መነሻው ከፍጹም ቅጣት ምት የሆነ ኳስ ተቆጥሮባቸው ጥረታቸው በአንድ ነጥብ ብቻ መቋጨቱ አስቆጪ ነበር። በ31 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ወደ 10ኛ ከፍ ያደርገዋል።

ከአምስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ አዳማ ከተማን ያሸነፉት ነጌሌ አርሲዎች ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ መለያየታቸው በጨዋታው ላይ የነበራቸውን ብልጫ የማይገልጽ ነበር። ቡድኑ በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ካባከነ በኋላ በተለይም 80ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀም ቀርቶ በመልስ ምት የተጀመረው ኳስ በጥቂት ሴኮንዶች ልዩነት የራሳቸው መረብ ላይ አርፏል። የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በመቻል መረታቱ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ከ6 ወደ 4 አለማጥበባቸው ቁጭታቸውን ይበልጥ የሚያጎላው ነው። ሆኖም በዛሬው ጨዋታም ድል ተቀዳጅተው መሪው ላይ  ጫና ለመፍጠር ጠንካራ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሸገር ከተማ በኩል ገዛኸኝ ደሳለኝ በቀይ ካርድ እንዲሁም ምስጋና ሚልኪያስ በ5  ቢጫ ካርዶች ቅጣት የማይሰለፉ ሲሆን ናትናኤል ዘለቀ ለጨዋታው የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። በነጌሌ አርሲ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ 2ለ2 መለያየታቸው ይታወሳል።

 

አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ባለፉት 6 ሳምንታት አንድ በማሸነፍ ከዛ ቀጣዩን በመሸነፍ ሂደት 3 አሸንፈው በሦስት ተሸንፈው አሁንም በ22 ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ጫፍ ከሚገኘው መድን በ7 ነጥቦች ርቀው ተቀምጠዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢኖሩም የወጥነት ችግር እየተስተዋለበት ያለው ቡድኑ በቀሪ 12 ጨዋታዎች ተደጋጋሚ ድሎችን  ማስመዝገብ በሊጉ ለመቆየት ትልቅ ዕድል የሚሰጠው ይሆናል።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ሀዲያ እና ኤሌክትሪክን በተመሳሳይ 2ለ1 ያሸነፉ ሲሆን ለዛሬው ጨዋታ በጥሩ መነሳሳት ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። በተለይም ለጨዋታ ምቹ ያልሆነውን የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በቶሎ በመላመድ እና በጥሩ ቅብብሎች ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ። ከአርባምንጭ (12) ቀጥሎ ከፍተኛውን የሽንፈት መጠን (10) ካስመዘገቡ አምስት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከዚህ ወጥተው ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ ካስቀጠሉ ባልተጠበቀ ጥሩ አጨራረስ ውድድሩን ሊያጠናቅቁ ይችላሉ።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ21 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ድል አድርጎ የተቀሩት 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።

 

መቐለ 70 እንደርታ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ከመጨረሻ 6 ጨዋታዎች በ 4 ተሸንፈው በ 2 አቻ የተለያዩት እና በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ውስጥ በደካማ ጉዞ የቀጠሉት ምዓም አናብስት በእነዚህ ጨዋታዎች በአጠቃላይ ከአንድ በላይ ግብ አለማስቆጠራቸው ደግሞ ትልቁ እንቅፋታቸው ነው። ከጨዋታ ጨዋታ በራስ መተማመኑን እያጣ የመጣው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ጫፍ ላይ ከሚገኘው መድን በ6 ነጥቦች የራቀ ሲሆን በቶሎ ወደ ውጤት ካልተመለሰ ፊቱ ላይ አደጋ ተደቅኖበታል። ሆኖም በዛሬው ጨዋታ ሌላኛውን በወራጅ ቀጠናው የሚገኘውን የክልሉን ተቀናቃኝ ቡድን እንደመግጠሙ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።

በጥሩ መሻሻል ላይ የነበሩት ወልዋሎዎች ከመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ግን 1 ነጥብ ብቻ ማግኘታቸው በድጋሚ ወደ ወራጅ ቀጠናው መልሷቸዋል። ከሀዋሳ ጋር በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሁለት ነጥቦችን ያጣው ቡድኑ በመጨረሻው ሳምንትም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ በወላይታ ድቻ 1ለ0 የተሸነፈ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ የሚያሳየውን ማራኪ አጨዋወት በድጋሚ ወደ ውጤት መቀየር ይኖርበታል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ 13ኛ ከፍ የሚያደርጋቸው ቢጫዎቹ ለወሳኙና ከማሸነፍ ውጪ አማራጭ ይዞ ከማይመጣው መቐለ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ የሚቀርቡበት መንገድ ይጠበቃል።

መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፉት ጨዋታዎች በህመም ምክንያት ካልተሰለፈው አሸናፊ ሀፍቱ በተጨማሪ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስን በቅጣት ምክንያት አያሰልፍም። በወልዋሎ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ 7 ጊዜ ተገናኝተው 2 ጊዜ አቻ ሲለያዩ መቐለ 3 ወልዋሎ ደግሞ 2 ጊዜ ድል አስመዝግበዋል። ምዓም አናብስት 6፣ ቢጫዎቹ ደግሞ 4 ጎል አስቆጥረዋል። (በመቐለ 70 እንደርታ አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ አልተካተተም)።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሽረ ምድረገነት

ከመጨረሻ 7 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት ይባስ ብሎም ከመጨረሻ 3 ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ የሰበሰቡት ሐይቆቹ ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክሩ እየራቁ እየመጡ ነው። ከመሪው ሲዳማ ቡና በ7 ነጥቦች ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ወቅታዊ ብቃቱ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው። በተለይም የቡድኑ መተማመኛ የነበረው ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀት በእነዚሁ 3 ጨዋታዎች ብቻ 7 ግቦችን ማስተናገዱ ለውጤት ማጣታቸው እንደ ትልቅ ምክንያት ይጠቀሳል። የዛሬ ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥረት እያደረገ ያለ ቡድን እንደመሆኑም ቀላል ፈተና ላይጠብቃቸው ይችላል።

ከመጨረሻ 5 ጨዋታዎች 2 ነጥቦችን ብቻ የሰበሰቡት እና በወቅታዊ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ሽረዎች ወሳኙ ሁለገብ ተጫዋቻቸው ሽመክት ጉግሳ ላይ የ6 ጨዋታዎች ቅጣት በመተላለፉ የሚያጡት ነገር ብዙ ነው። በተለይም በተጠቀሱት 5 ጨዋታዎች 2 ግቦች ብቻ ያስቆጠረውን የአጥቂ መስመር በራስ መተማመኑን በድጋሚ ለማምጣት የአንጋፋው ተጫዋች መኖር የሚያስፈልጋቸው ነበር። ቡድኑ በ28 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጡ ቶሎ ድሎችን ወደ ማሳካት መምጣት ይኖርበታል።

ሽረ ምድረ ገነት በዛሬው ጨዋታ ሸመክት ጉግሳን በቅጣት ፤ መክበብ ደገፉ፣ ብሩክ ሐድሽ እና ፀጋይ ፀሐይን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም። በተጨማሪም ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐይ ሜዳ ላይ ተገኝተው ቡድናቸውን አይመሩም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ 2 ጊዜ ፣ ሽረ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። ምድረ ገነት ሽረዎች 11 ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው 12 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።