ከሦስት ክለቦች ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ስኬታማ የሆኑት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት ተቃርበዋል።

ከኢትዮጵያ መድን ጋር የነበራቸው የውል ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ቀጣይ ማረፊያ የት ይሆናል የሚለው በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች የሚጠበቅ ዜና ሆኗል።
ትናንት ከኢትዮጵያ መድን የቦርድ አባላት ጋር በቡድኑ ለተጨማሪ ዓመት በሚቆዩበት ዙርያ ንግግር ቢያደርጉም አሰልጣኙ የመቆየት ሀሳብ እንደሌላቸው በመግለፅ በክብር ተለያይተዋል። ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ገብረመድህን ወዴት ያመራሉ የሚለውን ያጣራችው ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለት ክለቦች ጋር ስማቸው በስፋት እየተነሳ ቢገኝም እንደ ምንጮቻችን ከሆነ አሠልጣኙ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለማምራት ከጫፍ ደርሰዋል።
ትናንት እና ዛሬ ከኢትዮጵያ ቡና የቦርድ አባላት ጋር ያደረጉት ንግግር በአብዛኛው ነገሮች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሰማን ሲሆን የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር በቅርብ ጊዜ ውስጥ የቡናማዎቹ አሰልጣኝ መሆናቸው ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ከዚህ ቀደም በትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መቻል፣ ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑ ሲሆን ከጅማ አባጅፋር፣ መቐለ ሰባ እንደርታ እና ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሊጉን ዋንጫ ከፍ ማድረግ የቻሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዚህ ከቀደም ያሰለጠኑት ኢትዮጵያ ቡና ዳግም ለመረከብ ከጫፍ ደርሰዋል።

