ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ28ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ28ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ሊጉ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት የሚያደርጉት የ28ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች !

በቅርብ ሳምንታት አስደናቂ መሻሻል ካስመዘገቡ ክለቦች ውስጥ የሚጠቀሱት ፈረሰኞቹ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን ባሳኩባቸው መርሐ ግብሮች ያሳዩት እንቅስቃሴ ከአስከፊው ውጤት አልባ ጉዞ በሚገባ እንዳስንሰራሩ ያመለከተ ነበር። በሰላሣ ሁለት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ጠንካራውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀድያ ሆሳዕናን ባሸነፉበት እንዲሁም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረችባቸው ግብ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ካሳዩት ድንቅ የድል ረሀብ መንፈስ በተጨማሪ በማጥቃቱ ረገድ የነበራቸው ብልጫም ቡድኑ ላይ ከታዩ ጉልህ መሻሻሎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዛሬው ጨዋታም ባለፉት ሦስት መርሐ ግብሮች ስድስት ግቦችን በማሳረፍ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘውን የፊት መስመራቸው ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

ሰላሣ ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ ከዛሬ ተጋጣሚያቸው በአንድ ነጥብና አንድ ደረጃ ልቀው 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ካሉበት እጅግ አስከፊ ውጤት አልባ ጉዞ የሚያንሰራራ ድል ለማግኘት ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በመደዳ ሽንፈት የገጠማቸው አዳማ ከተማዎች ድል ካደረጉ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎችም ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥብ ማሳካት የቻሉት አምስቱን ብቻ ነው። በሁለተኛው መንፈቅ ጥቂት ነጥብ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ በርከት ያሉ መሻሻል የሚገባቸው ድክመቶች ቢኖሩትም የመከላከል አደረጃጀቱ ግን አንገብጋቢ መፍትሔ ይሻል። በመጨረሻዎቹ አምስት መርሐ ግብሮች በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ያስተናገደውን ክፍል ማሻሻልም ከቡድኑ ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ ሙጂብ ቃሲምን በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የማያገኝ ሲሆን የአጣማሪው መናፍ ዐወል መግባትም አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቁሟል። በተቃራኒው መድሃኔ ብርሃኔ ከቅጣት ሔኖክ ካሳሁን ደግሞ ከጉዳት ማገገማቸው ተሰምቷል። በተጨማሪም ከብሔራዊ ቡድን መልስ ጉዳት ላይ የሰነበተው ብዙዓየሁ ሰይፉም ማገገሙ ለአዳማ መልካም ዜና ሆኗል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሻይዱ ሙስጠፋ ከረጅም ጊዜ ህመሙ አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን አሚኑ ነስሩ ግን ከጉዳቱ ቢያገግምም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 47 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ 24 ጊዜ ድል ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 61 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው አዳማ ከተማ ደግሞ 35 ግቦችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ 13 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።