ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከማላዊ ጋር አቻው ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አስመልክቶ ተከታዩን ጥንክር እነሆ!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሰኔ ወር የፊፋ የብሔራዊ ቡድኖች የጨዋታ ወቅትን መነሻ በማድረግ ከማላዊ ጋግግ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ያለፉትን አራት ቀናት ዝግጅቱን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ከነገው የመጀመርያ ጨዋታ አስቀድሞ ጨዋታውን በሚያከናውንበት የድሬደዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ቀን ልምምዱን ሰርቷል።
– ትናንት ወደ ድሬደዋ የመጣው ብሔራዊ ቡድኑ ማምሻውን ልምምዱን ያከናወነ ሲሆን የከተማ መስተዳድሩ ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጆሀር እንኳን ደህና መጣቹሁ በማለት በማበረታታት የቡድኑን ልምምድ ተመልክተዋል።
– ቡድኑ ዛሬ ከአስር ሰዓት ተኩል ጀምሮ ዝግጅቱን ያከናወነ ሲሆን ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል።
– በዛሬው መርሀ ግብር አሰልጣኝ ዮሐንስ ቡድኑን ለሁለት ከፍለው ሙሉ ሜዳ ያጫወት ሲሆን በነገው ጨዋታ በመጀመርያ ቋሚ አስራ የሚጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ ሲያሰሩ አይተናል።
– የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ማለዳ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ድሬደዋ የገባ ሲሆን ከጉዞ መደራረብ ጋር ተያይዞ በቡድኑ አባላት ላይ ድካሞች ተስተውሏል። ቡድኑም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምድ መጠናቀቅ በኋላ የመጀመርያ ልምምዱን በዚሁ ሜዳ የሚያከናውን ይሆናል።

– ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች ዛሬ ከጅቡቲ ተነስተው በቀጥታ ድሬደዋ የሚያርፉ ሲሆን ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አለመድረሳቸውን ሲታወቅ አመሻሽ ላይ ድሬደዋ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
– በድሬደዋ ያለው የሙቀጥ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የጨዋታውንም ሰዓት ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት መሆኑን አውቀናል።
– የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የመገናኛ ብዙሀን ድሬ ቲቪ ጨዋታውን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጠዋል ወይስ በሌሎች አማራጮች ጨዋታው ይተላለፋል የሚለውን ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አሁን ላይ አልተሳካም።
– አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከዛሬው የመጨረሻ ልምምድ በኋላ ከጨዋታ አስቀድሞ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ የአሰልጣኙን ዋና ዋና ሀሳቦችን ከደቂቃዎች በኋላ ይዛ የምትመለስ ይሆናል።

