ወላይታ ድቻን ከነጌሌ አርሲ ያገናኘው የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ34ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት 0ለ0 ተጠናቋል።

በ34ኛው ሳምንት ሊደረግ መርሐግብር ወጥቶ በዝናብ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተራዝሞ በዛሬው እለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ወላይታ ድቻን ከነጌሌ አርሲ አገናኝቶ የተደረገው ተስተካካይ ጨዋታ በተመጣጣኝ ጨዋታ እንቅስቃሴ ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን ከደቂቃ ደቂቃ እየጠነከሩ የመጡት የጦና ንቦች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

በተለይም ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ ጨርፎ አሻግሮ ብቻውን ሆኖ ያገኘው ቸርነት ኡፋይሳ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው፣ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በፍጥነት ደርሶ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ መትቶ ዒላማውን ሳይጠብቅ የቀረው እንዲሁም ሳሊፉ ኢብራሂም ከርቀት አክርሮ መትቶ ከግቡ አናት ያለፋባቸው ሙከራዎች መሪ ሊያደርጓቸው የተቃረቡ የጦና ንቦች ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በረጃጅም ኳስ መግባትን ምርጫቸው ያደረጉት ሰጎኖቹ በአጋማሹ በመልሶ ማጥቃት ለመግባት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ኳሶች እየተቆራረጡባቸው በአጋማሹ ምንም አይነት ሙከራ ሳያደርጉ የጦና ንቦችን አንፃራዊ ብልጫ ያሳየን አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርበት ተገባዶ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አጨዋወት ተመልሰዋል። በዚህም ወላይታ ድቻዎች ወደፊት እየገቡ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጠንካራ ሙከራ አላስመለከቱንም። ነጌሌዎቹ በበኩላቸው የተጫዋች ቅያሪ አድርገው በመስመር በኩል ወደ ፊት ለመግባት ጥረት ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ግን ጨዋታዎች ግባ ሳይቆጠርበት ነጥብ በማጋራት 0ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

