ወላይታ ዲቻዎች የሁለት ተጫዋቾች ውል ለማራዘም ተስማምተዋል

ባለፈው የውድድር ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ አስደናቂ መነቃቃት በመፍጠር የሊጉን ማጠናቀቂያ ደረጃቸውን ወደ 7ኛነት ማሻሻል የቻሉት ወላይታ ዲቻዎች ለአዲሱ የውድድር ዘመን ያግዛቸው ዘንድ ወደ ዝውውር መስኮቱ ገብተዋል። በቅርቡ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ውል በማደስ የአሰልጣኝ ክፍሉን ያደላደለው ክለቡ አሁን ደግሞ በቀጣይ ዓመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ስብስቡን የማጠናከር ስራ ላይ በስፋት ተጠምዷል። ይህንን ተከትሎም በክለቡ ቁልፍ ሚና የነበራቸውን ተጫዋቾች ለማቆየት ከስምምነት ደርሰዋል።
በዚህም የወጣት ቡድኑ ፍሬ የሆነው አማካዩ መሳይ ኒኮል እና ከዚህ ቀደም በመቻል ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በክለቡ ቆይታ የነበረው አማካዩ ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከቡድኑ ጋር ለመቀጠል ከስምምነት ደርሰዋል።

