የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሐምሌ 4 ወደ አሜሪካ ተጉዞ የሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ እንደማይካሄድ ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለፉትን ዓመታት ወደ ሀገረ አሜሪካ አምርቶ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረጉ ይታወሳል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ባደረገው ስምምነት በየዓመቱ ቡድኑ ወደ አሜሪካ እየሄደ ጨዋታዎችን የሚያደርግ ሲሆን ዘንድሮም በሐምሌ ወር መጀመሪያ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ስፍራው ተጉዞ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ተገልፆ ነበር። ዲሲ ዩናይትድም በይፋዊ ድህረ ገፁ የስታዲየም ትኬቶች እየሸጠ የነበረ ሲሆን ዛሬ በተሰማ መረጃ ግን ይህ ጨዋታ መሰረዙ ታውቋል።

ብሔራዊ ቡድናችንን የሚጋብዘው ዲሲ ዩናይትድ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ሐምሌ 4 እንዲደረግ ታስቦ የነበረው ጨዋታ በምስራቅ አፍሪካ እንደ አዲስ እየተስፋፋ በመጣው የኢቦላ ቫይረስ ምክንያት ቪዛ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሆነ ተመላክቷል።
ይህንን ተከትሎ የስታዲየም መግቢያ ትኬይ ሽያጭ የቆመ ሲሆን ትኬት ቀድመው ለገዙም ከ3 እስከ 7 ቀናት ውስጥ ተቋሙ ሙሉ ለሙሉ ገንዘብ ተመላሽ እንደሚያደርግ ገልጿል።

