👉”ሀገር ወክለን እንደ መቅረባችን እንዲሁም ካለብን ችግሮች አንፃር ድጋፍ እንሻለን”
👉”ላሳያችሁኝ ፍቅርና ክብር ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው”
👉”የወልዋሎ 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በእግር ኳሱ የነበረንን ስኬት ዳግም ለመመለስ በአከባብያችን የስፖርት መነቃቃት ለመፍጠር እና አጠቃላይ የክለባችን አካሄድና አወቃቀር ለመቀየር መሰረት የምንጥልበት ይሆናል”

በቅርቡ የ70ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓላቸውን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንዳሉ የገለፁት እና በቀጣይ የውድድር ዓመት ኢትዮጵያን ወክለው በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን የሚካፈሉትን ወልዋሎች ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ አንገሶም ተክላይ በክለባቸው የ70ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር ፣ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክተው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ስለ 2018 ውድድር ዓመት ጉዟቸው ?
በብዙ ፈተናዎች የታጀበ ከባድ ዓመት ነው ያሳለፍነው። አጀማመራችን ደካማ ነበር በሁለተኛው ዙር ግን ድክመታችን አርመን ትላልቅ ስኬቶች አግኝተናል። ከነበረው ከባድ ፉክክርና ቡድናችን ካለፋቸው ችግሮች አንፃር ሲታይ በሊጉ መትረፋችን ትልቅ ስኬት ነው በስተመጨረሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ዋንጫ በማንሳት ዓመቱን አጠናቀል። ጠቅለል አድርገን ስናየው በብዙ ነገር መሻሻል ይገባናል በዚህ ዓመት ያሳካናቸው ነገሮች ደግሞ መነሻ ይሆኑናል ብዬ አስባለሁ። በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾቻችን ፣ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እንዲሁም ደጋፊዎቻችን በከባዱ የውድድር ዓመት ላበረከቱት ትልቅ አስተዋፅዖ በክለቡ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ።
ስለ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳትፎ ?
በአፍሪካ ውድድር መሳተፍ በፕሪምየር ሊጉ ከመቆየት ቀጥሎ የያዝነው ዕቅድ ነበር። ክለባችን በኔ የፕሬዚደንትነት ዘመን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ውድድር መብቃቱ በጣም ደስተኛ ነኝ ግን የሚጠብቀን ፈተና እጅግ በጣም ከባድ ነው። በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ብቁ ሆነን ለመቅረብ ከወዲሁ እየተዘጋጀን ነው ፤ ሆኖም ሀገር ወክለን እንደ መቅረባችን እንዲሁም ካለብን ችግሮች አንፃር ድጋፍ እንሻለን።
ትግራይ እንዲሁም የትግራይ እግር ኳስ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ይታወቃል የትግራይ ክለቦች በከባድ ሁኔታ ተፈትነው ነው ዓመቱን ያጠናቀቁት። በቀጣይ ኢትዮጵያን ወክለን በምንሳተፍበት የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የተሻለ ጉዞ ለማድረግም መንግስት ፣ ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም ባለ ሀብቶች እንዲያግዙን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እፈልጋለሁ።
ወልዋሎ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የፋይናንስ ችግር ከገጠማቸው ክለቦች አንዱ ነው ፤ የችግሩ መንስዔ ምን ነበር በቀጣይስ ምን አስባቹሃል ?
በፕሪምየር ሊጉ ለመሳተፍ የሚወጣው ወጪ በጣም ብዙ ነው። የሜዳ ገቢ ፣ በቂ የሆነ የማልያ ሽያጭ እና የስፖንሰር ሺፕ ገቢዎች እንዲሁም ተያያዥ የፋይናንስ አቅምህን የምታጎለብትባቸው ገቢዎች ሳይኖሩ በሊጉ መሳተፍ በጣም በጣም ከባድ ነው። ስለዚ የምትጠብቀው ከከተማ መስተዳደር እና ከባለ ድርሻ አካላት የሚገኘው በጀት ነው እሱም እንደ ልብ አይገኝም። ችግሩ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክለብ የከተማ አስተዳደሮች ጥገኛ መሆናችን ነው። በቀጣይም ክለቡ ከዚህ ችግር ለማላቀቅ በዘመናዊ መንገድ በማዋቀር ራሱን በራሱ የሚያስትዳድርበት አቅም ለመገንባት ወደ ኢንተርፕራይዝ የመቀየር እቅድ አለን። አሁን ባለው የእግር ኳሳችን ሁኔታ ከባድ ቢሆንም የተሻለ መፍትሔ ነው ብዬ አምናለሁ። በቀጣይ ዓመት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩም ከወዲሁ የፋይናንስ ዓቅማችን ለማጠናከር እየሰራን ነው።
ስለ ክለቡ ቀጣይ ዕቅዶች
በረዥም እና በአጭር ጊዜ ለማሳካት ያቀድናቸው ብዙ ስራዎች አሉ በቀዳሚነት የያዝነው ግን በሂደት ከመንግስት የበጀት ጥገኝነት መላቀቅ ነው። ከደጋፊዎቻችን እንዲሁም በክለባችን ዙርያ ካሉት ባለ ሀብቶች ጋር ተባብረን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በመስራት የፋይናንስ አቅማችንን ማጎልበት ቀዳሚው ዕቅዳችን ነው። ዓድግራት እና አከባቢው ጥሩ የስራ ባህል ያለው ህዝብ ያለበት እንዲሁም የእግር ኳስ ፍቅር ያላቸው ብዙ ባለ ሀብቶች ያለበት አከባቢ ነው። ቦርድ ውስጥ እኔን ጨምሮ ያወጣቸውን ማሕበረሰብ በተለያየ መንገድ መገደፍ የሚፈልጉ ባለ ሀብቶች አሉ ፤ አጠቃላይ ያለንን ፀጋ ተጠቅመን ክለቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ነው እቅዳችን። በተጨማሪም አጠቃላይ የክለቡን አደረጃጀት ማዘመን የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሁም በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር ክለቡን ማዋቀር እቅድ አለን።
ወልዋሎ ሳቢ የሆነ ደጋፊዎችን የሚያዝናና የጨዋታ መንገድ ያለው ከሀገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ትልቅ ‘Fun base’ ያለው ክለብ ለማድረግ እንፈልጋለን። በርግጥ እነዚህ ስራዎች ለመስራት ብዙ ጥረት እና ‘Investment’ ይጠይቃል ግን ብያንስ መሰረቱን ጥለን በረዥም ጊዜ ዕቅድ ማሳካት እንችላለን ብለን እናምናለን።
በቀጣይ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ የተሻለ ተፎካካሪ መሆን የሚችል እንዲሁም በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን የተሻለ ጉዞ ማድረግ የሚችል ቡድን መገንባት ደግሞ የአጭር ጊዜ እቅዳችን ነው። በሁሉም ረገድ የተሻለ ቡድን ለመገንባት እየተዘጋጀን ነው። የኢትዮጵያ ዋንጫ ማሸነፋችን ተከትሎ በደጋፊዎቻችን የተደረገልን አቀባበል እና የተሰጠን ምላሽ ልብ የሚሞላ ነው። ይህም ለቀጣይ ጠንክረን እንድንሰራ ያደርገናል ፤ በዚህ አጋጣሚ አቀባበል ያደረገልን መላው የስፖርት ቤተሰብ ማመስገን እፈልጋለሁ።
ስለ ክለባቸው የ70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር
1948 የተመሰረተው ክለባችን ዘንድሮ 70ኛ ዓመቱን ደፍኗል። ክብረ በዓሉ በኢትዮጵያ ዋንጫ ድል መታጀቡ ልዩ የሚያደርገው ሲሆን እስከ መስቀል በዓል ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የክለባችን ምስረታ ማክበር ፣ በክለባችን ታሪክ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ግለ ሰቦችና ተቋማት ማክበር እና እውቅና መስጠት ከዚህ ባሻገርም የክለባችን የፋይናንስ አቅም የሚያጎለብቱ ዝግጅቶች ለማዘጋጀት አቅደናል። ዓድግራት በብሔራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ የተጫወቱ እንዲሁም በክለብ አመራርነት እና በዳኝነት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው እንደነ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ፣ ታደሰ ገ/ማርያም ፣ ሰለሞን ባጥራን ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሰፋ ገሰሰ እንዲሁም አይናለም ሃይለ እና ሌሎች በርካታ የስፖርት ባለሞያዎች ያፈራ የእግር ኳስ አከባቢ ነው። የወልዋሎ 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በእግር ኳሱ የነበረንን ስኬት ዳግም ለመመለስ በአከባብያችን የስፖርት መነቃቃት ለመፍጠር እና አጠቃላይ የክለባችን አካሄድና አወቃቀር ለመቀየር መሰረት የምንጥልበት ይሆናል።

በመጨረሻም ክለባቹህ ሲዳማ ቡናን አሸንፎ የኢትዮጵያ ዋንጫ ባነሳበት ቀን የብዙዎችን ትኩረት ስለሳበው የደጋፊዎች መልዕክት እናንሳ … ?
ሀገር ውስጥ ስላልነበርኩ አጋጣሚ ጨዋታው በሜዳ ተገኝቼ አልተከታተልኩም። መጀመሪያ ሳየው
ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ ደጋፊዎች የኔ ምስል ያለበት ትልቅ ባነር ይዘው ሲያመሰግኑኝ ደስ ብሎኛል። በዚህ አጋጣሚ ላሳያችሁኝ ፍቅር ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው ፤ ታሪካዊውን ክለብ ተባብረን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምናሸጋግረውም እምነት አለኝ። በስራ ምክንያት ዓድግራት በነበረው ደማቅ አቀባበል መገኘት ባልችልም የቡድናችን አባላት በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ደስ ብሎኛል።

