ድሬዳዋ ከተማ ሸገር ከተማን 2ለ0 በማሸነፍ ከረጅም ሳምንታት በኋላ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።

የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ ጨዋታ በአዳማ ከተማ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከሸገር ከተማ አገናኝቷል። የጨዋታው ጅማሮ ላይ አደገኛ የሸገሮችን ሙከራ አስመልክቶ የቀጠለው ጨዋታ 19ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ብርቱካናማዎቹን መሪ አድርጓቸዋል።

አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ወደፊት ይሄዱ የነበሩት ሸገር ከተማዎች በሀያ ዘጠነኛው ደቂቃ በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ ቋሚ ብረት ርቆ ያለፈበት አደገኛው ሙከራ ይጠቀሳል። የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ አብዲሳ ጀማል ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው ብርቱካናማዎቹን መሪነታቸውን አጠናክረው እንዲወጡ ሊያደርጋቸው የተቃረበ አስቆጪ አጋጣሚ እየተጠቀሰ ለእረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ሸገር ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በሚያደርጉት እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። በዛው ውጤት የሚያልቅ ቀጥሎ 84ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስመልክቶናል። የቆመ ኳስ ያገኙትን አብዱሰላም የሱፍ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ ለብርቱካናማዎቹ እፎይታ ሰጥቶ ጨዋታው 2ለ0 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።


