የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ካሮል ካንያምባ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሰጠችው አስተያየት

የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ካሮል ካንያምባ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሰጠችው አስተያየት

👉 ” አንድም ዕድል አናሳልፍም በሚል ወደ ጨዋታው ገብተን ውጤታማ መሆን ችለናል”

👉 “ትልቁን ምስጋና ለተጫዋቾቼ አቀረባለሁ፤ ከመጀመሪያዋ ደቂቃ እስከ መጨረሻዋ ድረስ በከፍተኛ ተነሳሽነት ተዋግተዋል።”

👉 “ኢትዮጵያ ጠንካራ ተፎካካሪ ነበረች፤ እኛ ግን በሜዳችን የነበረንን ክፍተት ዘግተን በመግባት ታሪክ ሰርተናል።”

በአለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በድምር ውጤት 3 ለ 2 በሆነ ውጤት የኢትዮጵያን አቻውን አሸንፎ ወደ አለም ዋንጫው ማለፉን ማረጋገጡ ይታወቃል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዛምቢያዋ ዋና አሰልጣኝ ካሮል ካንያምባ ለጋዜጠኞች በሰጠችው መግለጫ ላይ ያነሳቻቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ሶከር ኢትዮጵያ እንደሚከተለው አሰናድታዋለች።

“በመጀመሪያ ይህንን ድንቅ ድልና ማለፍ ላሳካልን ፈጣሪ ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ” ያለችው አሰልጣኟ፣ ጨዋታው ቀላል እንደማይሆን አስቀድማ እንደምታውቅ ገልጻለች። አክላም፦ “ትናንትም እንደተናገርኩት ጨዋታው ቀላል አልነበረም። ነገር ግን እኛን ሳይዘጋጅ ለሚመጣ ማንኛውም አጋጣሚ አንድም እድል ሳናሳልፍ በጥንቃቄ ለመጫወት ወስነን ነበር የገባነው። ለዚህም ነው ሙሉ ምስጋናዬን ለሴት ልጆቼ ማቅረብ የምፈልገው። ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስቶ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በቁርጠኝነት ተዋግተዋል” ብላለች።

ቡድኑ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ወደ አለም ዋንጫ ማለፉ ምን ትርጉም አለው ተብላ ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ፦ “ይህ የሚያሳየው የቡድኑን ወጥነት (consistency) ነው። ነገሮችን በተከታታይነት በጥሩ ሁኔታ ስታከናውን የቡድኑ እድገት ከፍ ይላል። ይህም በሀገር ውስጥ ላሉ ሌሎች ተጫዋቾች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥርና ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ለመምጣት እንዲታገሉ የሚያደርግ ነው” ስትል ገልጻለች።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቡድን በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ የፈጠረውን ከፍተኛ ጫና እንዴት እንደተቋቋሙት ስታስረዳ፦ “ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ቡድን ናት። በተለይ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ እኛ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ማጥቃት ጀምረው ነበር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ለተጫዋቾቼ የነገርኳቸው ነገር ቢኖር በእርጋታ የራሳቸውን ጨዋታ እንዲጫወቱና በነበረን የዕረፍት ሰዓት የተነጋገርናቸውን ታክቲካዊ መመሪያዎች እንዲተገብሩ ነበር፤ እነሱም ይህንን በአግባቡ በመወጣት ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል” ስትል አስተያየቷን ቋጭታለች።