በልማት ካፕ የፉትሳል ውድድር የአንድ ተጫዋች ዐይኑ ክፉኛ መጎዳቱ ተሰምቷል

በልማት ካፕ የፉትሳል ውድድር የአንድ ተጫዋች ዐይኑ ክፉኛ መጎዳቱ ተሰምቷል

በልማት ካፕ ዓመታዊ የፉትሳል ውድደር ላይ የአንድ ተጫዋች የቀኝ ዐይን ክፉኛ መጎዳቱ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከፍ ባሉ የሊግ ውድድሮች ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ዓመታዊ የሰመር ካፕ የፉትሳል ውድድር ዘንድሮም በአርባምንጭ ከተማ በደማቅ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል። ትናንት በተከናወነ ጨዋታ አንድ ተጫዋች የቀኝ ዐይን ክፍሉ ክፉኛ መጎዳቱን ሰምተናል። ተጫዋቹ ፀጋአብ ማንያዘዋል ሲባል በስፍራው የነበረ የስፖርት ቤተሰብ እና አብረውት ይጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች በመደናገጥ በሀዘን፣ በእንባ ስሜት ሆነው በፍጥነት ወደ አርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ቢወስዱትም ሐኪሞቹ ሕመሙ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለተሻለ ሕክምና ወደ ቅዱስ ጳውሎስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎለት በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ሕክምናውን እየተከታተለ ይገኛል።

ሆኖም ሶከር እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በሚያሳዝን ሁኔታ የተጫዋቹ ዐይን ክፉኛ መጎዳቱን ተከትሎ የቀኝ ዐይኑ የማየት ዕድሉ የጠበበ እንደሆነ ሰምተናል።

በአርባምንጭ ከተማ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ፀጋአብ ዘንድሮ በአንደኛ ሊግ ለኮንሶ ኒውዮርክ እየተጫወተ ይገኝ ነበር። ተጫዋቹን ለመደገፍ በቀጣይ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሠሩ ወንድሙ የነገረን ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ በቀጣይ አስፈላጊውን መረጃ ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል።