መቻል የሁለት ተጫዋቾች ተገቢነት ክርክርን ሲያሸንፍ ተጫዋቾቹ በበኩላቸው የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ ተጫዋች አለምብርሃን ይግዛው እና ተጫዋች አብዱልከሪም ወርቁ ከመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ እና ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ጋር ያደረጉትን የቅድመ ውል ስምምነት ውዝግብ መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን ታውቋል። ኮሚቴው የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎች እና የተጫዋቾቹን ቃል መርምሮ ተከታዮቹን ውሳኔዎች አሳልፏል።
በዚህም ተጫዋቾቹ የመጀመሪያውን ቅድመ ውል የፈረሙት ከመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ ጋር በመሆኑ በፊፋ መመሪያ እና በፌዴሬሹኑ ደንብ መሠረት የመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ ህጋዊ ባለቤት መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል። ከተጫዋቾቹ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሁለቱም ተጫዋቾች ከሁለት የተለያዩ ክለቦች ጋር ድርብ ውል በመፈረማቸው ጥፋተኛ ሆነው ተግኝተዋል። በመሆኑም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚጀምርበት ቀን ጀምሮ ለ4 ወራት ከማንኛውም ይፋዊ የእግር ኳስ ጨዋታ እንዲታገዱ ተወስኖባቸዋል። በተጨማሪም ሁለቱም ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 200,000 ብር የገንዘብ መቀጮ የተጣለባቸው ሲሆን እገዳቸው ከማለቁ በፊት ገንዘቡን ገቢ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።
ፌዴሬሽኑ እንዳለው ከሆነ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቅድመ ውሉን የፈረመው ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ እና ተጫዋቾቹ ቀደም ብለው ከሌላ ክለብ ጋር መፈረማቸውን ሳያውቅ በመሆኑ ከማንኛውም ቅጣት ነፃ ሆኗል። ሆኖም ለዝውውሩ ያወጣው ወጪ ካለ ከተጫዋቾቹ እንዲተካለት የመጠየቅ መብቱ እንደተጠበቀለት ተመላክቷል።

