ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት የዩጋንዳውን የሴቶች ክለብ ሲያሰለጥኑ የነበሩት አሠልጣኝ ፍሬው ውላቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው ይፋ ሆኗል።
በተለያዩ የእድሜ እርከን ቡድኖች የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድኖችን ያሰለጠኑት አሠልጣኝ ፍሬው ከሁለት አመታት በፊት ከሀገር ወጥተው የዩጋንዳውን ካምፓላ ኩዊንስ ክለብ ማሰልጠን እንደጀመሩ አይዘነጋል። በወቅቱ የሁለት አመት ውል አስረው ስራቸውን የጀመሩት አሠልጣኙ በመጀመሪያ አመታቸው የሊጉን ዋንጫ ያነሱ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ የፉፋ የሴቶች ዋንጫን ማሸነፍ ችለዋል። ታዲያ ከቀናት በፊት የክለቡን 30% ድርሻ በገዛው ኬሲሲኤ (KCCA FC) ስሙ እና ሎጎው የተቀየረው ካምፓላ ኩዊንስ ከኢትዮጵያዊው አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ጋር መለያየቱን በይፋ አስታውቋል።
ከለውጡ በኋላ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ክለቡ በቅርቡ አዲስ አሠልጣኙን የሚያሳውቅ ሲሆን ወደ ገበያውም በገፍ ገብቶ ስብስቡን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት አሠልጣኝ ፍሬው በቅርቡ ወደሌላ የምስራቅ አፍሪካ ክለብ ለማምራት ንግግር ጀምረዋል።

