የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምን መልኩ ሊካሄድ ይችላል ?

የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምን መልኩ ሊካሄድ ይችላል ?

የ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ፎርማት በቀጣይ ቀናት ይፋ ይደረጋል። እኛም በምን መልኩ ሊካሄድ እንደሚችል እንደሚከተለው ዳስሰናል።

ከአንድ ወር በኋላ መስከረም 30 የሚጀምረው እና በ18 ቡድኖች መካከል የሚደረገው የ2019 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምን መንገድ እንደሚቀጥል እስካሁን ያልተወሰነ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ባሉት ቀናቶች አወዳዳሪው አካል በይፋ እንደሚያሳውቅ እንዲሁም ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ የውድድሩ መርሐግብር ይፋ እንደሚደረግ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ የውድድር ሜዳ ሲካሄድ የነበረው ሊጉ በ2018 የውድድር ዘመን ግን በተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት በሁለት ሜዳዎች ተደርጓል። ሆኖም ለቀጥታ ሥርጭት አመቺ የሆነው ይህ በአንድ ሜዳ ላይ የሚደረግ ውድድር ደጋፊዎች ከሜዳ ያራቀ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ትችት ይቀርብበታል። ከዛም በተጨማሪ ሌላው አሳሳቢ ሆኖ የተስተዋለው በጨዋታዎች መብዛት ምክንያት የሜዳ መጎዳት እና ከጊዜያት በኋላ ተበላሽቶ ለጨዋታ አመቺ አለመሆን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነበር።

ለ2019 የውድድር ዓመት ሜዳ ያላቸው ቡድኖች ጨምሮ ባሕርዳር ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ሀላባ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ሜዳችን ለውድድር ዝግጁ ስለሆኑ የሜዳ ጨዋታችንን ባዘጋጀነው ሜዳ እናካሂዳለን ሲሉ ዝግጁነታቸውን አሳውቀዋል። ይህንን ተከትሎም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ውድድሩ በምን ፎርማት እንደሚቀጥል ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ሊሆኑ ይችላሉ ያለቻቸውን ውሳኔዎች እንደሚከተለው ዳስሳለች።

የመጀመሪያው በየሜዳቸው ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ እንዲሁም ሜዳ የሌላቸው ቡድኖች በመቀመጫ ከተማቸው ወይም በአቅራቢያው የሚመርጡትን ሜዳ እንደራሳቸው አስመዝግበው ውድድራቸውን ማካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ባለፈው ዓመት እንደነበረው ዘጠኝ ዘጠኝ ሆነው በሁለት ምድብ ተከፍለው በአንድ ከተማ ሲያደርጉ የነበረው ውድድር ማስቀጠል ሦስተኛው በአዲስ መልክ ለሦስት ተከፍለው ስድስት ቡድኖች ሆነው በሦስት ሜዳዎች ማድረግ እንደ አማራጭ ቀርቧል። እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ በሦስት ሜዳ ለሦስት ተከፍለው ውድድሩን የማስኬድ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ሰምተናል።