ካፍ የጨዋታ ሕጎች ላይ ማሻሻያዎች አደረገ

ካፍ የጨዋታ ሕጎች ላይ ማሻሻያዎች አደረገ

በካፍ አህጉራዊ ውድድሮች ተግባራዊ የሚሆኑ ሕጎች ምን ምን ናቸው ፤ አፈፃፀማቸውስ ?

በቅርቡ በተካሄዱት የ2026 የዓለም ዋንጫ እና የ2026 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የሚባክነውን ጊዜ ለቀነስ ያለሙ አዳዲስ የሕግ ማሻሻያዎች ተፈፃሚ መሆናቸው ይታወሳል።

የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ካፍም በዛሬው ዕለት ከሚጀመሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ የተሻሻሉ የጨዋታ ሕጎች የደነገገ ሲሆን በቅድመ ጨዋታ ውይይት ላይም ለተሳታፊ ክለቦች ሕጎቹን የተመለከተ ሰፊ ማብራርያ ተሰጥቷል። ማሻሻያ የተደረገባቸው ሕጎች እና አፈፃፀማቸውም እንደሚከተለው ተገልጸዋል።

​1. የእጅ ውርወራ እና የመልስ ምት፦ የአምስት ሰከንድ ቆጠራው የሚጀምረው ዳኛው ፊሽካ ሲነፋ ወይም ዳኛው ለተጫዋቹ ጨዋታውን እንዲጀምር ምልክት ሲሰጥ ነው። ተጫዋቹ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ካሳለፈ ለተቃራኒ ቡድን የእጅ ውርወራ ይሰጣል፤ ወይም ለዘገየ የመልስ ምት ለአጥቂው ቡድን የማዕዘን ምት ይሰጣል።

​2. ተጫዋች መቀየር ፦ ተጫዋቾች ቁጥራቸው በቅያሪ ማሳያ ‘ቦርድ’ ላይ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ በ10 ሰከንዶች ውስጥ ከሜዳ መውጣት አለባቸው። ተጫዋቹ ይህንን ሳያከብር ቢቀር ተቀይሮ የሚገባው ተጫዋች ከሜዳ ውጭ ይቆይ እና እንዲገባ እስኪፈቀድለት ድረስ ቢያንስ ለ1 ደቂቃ ቡድኑ በአንድ ተጫዋች ጎድሎ ለመጫወት ይገደዳል።

​3. የጉዳት ጉዳይ:- የህክምና እርዳታ የሚፈልግ ወይም በጉዳት ምክንያት ጨዋታ እንዲቆም የሚያደርግ ማንኛውም ተጫዋች ለ1 ደቂቃ ያህል ከሜዳ ውጭ መቆየት አለበት። ከዚህ ህግ ነፃ የሚሆኑት፦

.​ጥፋቱ የዲሲፕሊን ቅጣት (ካርድ) የሚያሰጥ ሲሆን
. ​የግብ ጠባቂ ጉዳት ሲሆን
. ​ጉዳቱ በቡድን አጋሮች መካከል በሚደርስ ግጭት ምክንያት ሲሆን ብቻ ነው።

​4. አፍን መሸፈን ፦ አንድ ተጫዋች ከባላጋራ ቡድን ጋር በሚኖረው ግንኙነት አፉ በእጁ በመሸፈኑ ብቻ የተሳሳተ የቀይ ካርድ ውሳኔ እንዳይከሰት ዳኛው ቀይ ካርድ ማሳየት ያለበት የጨዋታው ዳኞች ድርጊቱን እንደ ግጭት ፈጣሪነት ወይም ፀብ አጫሪነት አድርገው ሲወስኑ ብቻ ነው።

​5. ዳኛውን መክበብ፦ በጨዋታ ዳኞች ላይ ያልተገባ/የመናቅ ባህሪ የሚያሳይ ማንኛውም ተጫዋች፣ ተቀያሪ ወይም የቡድን አባል እንደ ድርጊቱ ከባድነት ወዲያውኑ መቀጣት አለበት። ይህም ከጨዋታው በኋላ እና በጨዋታው ሜዳ ዙሪያ ሚደረጉ ድርጊቶችንም ያካትታል።