ያለፉትን ሦስት ሳምንታት በመዲናችን አዱስ አበባ ሲዘጋጁ የቆዩት ዋልያዎቹ ወደ ሌላ ከተማ ሊያቀኑ ነው

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመስከረም ወር ሊሚያደርጋቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝግጅት ከጀመረ ዛሬ 22ኛ ቀኑን ይዟል። ለአርባ ተጫዋቾች ጥሪ ቢያደርግም በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ስብስቡን ማግኘት ያልቻለው ብሔራዊ ቡድኑ ላለፉት ሳምንታት 21 ተጫዋቾችን በመያዝ በመዲናችን አዲስ አበባ ልምምዱን በማከናወን ላይ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት ልምምዱን እንደሚቀጥል ታውቋል።
በትናንትናው ዕለት ከፈረሰኞቹ ጋር ያደረገው የመጀመርያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ቡድኑ ዛሬ ረፋድ የ22ኛ ቀን ልምምዱን ያከናወነ ሲሆን ነገ ወደ ሀዋሳ ከተማ እንደሚያቀና ሰምተናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መስከረም 13 በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ከሱዳን ጋር ከአምስት ቀን በኋላ መስከረም 19 ደግሞ በውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ከሴኔጋል ጋር የሚጫወት ይሆናል።

